የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ለመዘገብ እስከ አሁን 340 የውጭ አገራት ጋዜጠኞች አዲስ አበባ ገብተዋል

255

ጥር 26/2014/ኢዜአ/ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ለመዘገብ እስከ አሁን 340 የውጭ አገራት ጋዜጠኞች አዲስ አበባ መግባታቸውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ገለፀ።

40ኛው የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ዛሬ ሲጠናቀቅ 35ኛው የመሪዎች ጉባኤ ደግሞ የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ይካሄዳል።

የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ “የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፣ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ማፋጠን” በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።

ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት በኋላ መሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው በሚመክሩበት በዚህ ጉባኤ ላይ በመገኘት የሚዘግቡ 340 የውጭ አገራት ጋዜጠኞች አዲስ አበባ መግባታቸውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ገልጿል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ፤ የህብረቱን የመሪዎች ጉባኤ ለሚዘግቡ ጋዜጠኞች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባባር ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።

በተለይም ከውጭ ለሚመጡ ጋዜጠኞች ከቪዛ ጀምሮ ባጅ መስጠትና ሌሎች ለመዘገብ የሚያስችሏቸውን ሁኔታዎች አመቻችተናል ብለዋል።

ከአፍሪካ ህብረት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢምግሬሽንና ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በጋራ መስራታቸውን ጠቅስው እስካሁን ከሀገር ውስጥና ከውጭ ከ700 በላይ ጋዜጠኞች ለመዘገብ የሚያስችላቸውን ባጅ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ ቀናት ሌሎች ተጨማሪ የውጭ አገራት ጋዜጠኞችም ለተመሳሳይ ዓላማ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

የጋዜጠኞቹ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በአንዳንድ የምእራቡ ዓለም አገራት ሲራገብ የነበረውን የተሳሳተ መረጃ ተገንዝበው ያለውን ተጨባጭ እውነታ የሚዘግቡበት ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም