የጤና ሚኒስቴር የኩላሊት እጥበት የሚሰጡ ማሽኖችን ለክልሎች ሊያከፋፍል ነው

120

ጥር 26/2014/ኢዜአ/ የጤና ሚኒስቴር የኩላሊት እጥበት የሚሰጡ 13 ማሽኖችን ለክልሎች እንደሚያከፋፍል አስታወቀ።

የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ማህበር የገቢ ማሰባሳቢያ መርሃ-ግብር በዛሬው እለት ያስጀመረ ሲሆን፤ በዚህም ማህበሩ 10 ሚሊዮን ብር የመሰብሰብ እቅድ ይዟል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ኤርሚያስ ሙላቱ በዚህን ወቅት ሚኒስቴሩ በአገሪቱ ያሉ የኩላሊት ህመምተኞችን ችግር ለመቀነስ ለክልሎች የሚውል የ13 የኩላሊት እጥበት ማሽኖች ግዢ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡

ማሽኖቹም በቀጣይ ለሁሉም ክልሎች የሚከፋፈሉ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

በአሁኑ ሰዓት 35 የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚሰጡ የመንግስትና የግል ሆስፒታሎች ቢኖሩም የችግሩ አሳሳቢነት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዳግማዊ ሚኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል 30 የኩላሊት እጠበት የሚሰጡ ማሽኖችን በማስገባት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በአገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኩላሊት ህመምተኞች ቁጥር ለመቀነስ ሰፊ የግንዛቤ የማስጨበጫ ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ተቋርጦ የነበረው የነጻ የኩላሊት ንቅለ ተከላ በቅርቡ በድጋሚ እንደሚጀመርም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ፤ በገቢ ማሰባሰቢያው ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።

"ፎኖት ሮተሪስ" የተሰኘ ድርጅት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ለማህበሩ ድጋፍ ማድረጉንም ጨምረው ገልጸዋል።

የኩላሊት ህመም ታካሚ የሆኑት አቶ አበባው ጌታቸው በበኩላቸው ፤በሽታው የብዙ ኢትዮጵያውያንን ህይወት እየቀጠፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት ለችግሩ እየሰጠ ያለውን ምላሽ አድንቀዋል፡፡

የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ማህበር ከተቋቋመ 9 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በዘውዲቱ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም