ኢትዮ ቴሌኮም በአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ እየተሳተፉ ለሚገኙ እንግዶች የተለያዩ አገልግሎቶችን በዶላር፣ በዩሮና ድርሀም እያቀረበ ነው

89

ጥር 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮ ቴሌኮም በአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ እየተሳተፉ ለሚገኙ አካላት የተለያዩ አገልግሎቶችን በዶላር፣ በዩሮና ድርሀም እያቀረበ እንደሚገኝ አስታወቀ።

ኢትዮ ቴሌኮም በ40ኛዉ የአፍሪካ ሕብረት ስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤትና በ35ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች ባረፉባቸው ሆቴሎች፣ በቦሌ አለም አቀፍ አየር መንገድና በአፍሪካ ሕብረት ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝ የድርጅቱ በኤምባሲና በአለም አቀፍ ተቋማት የፕሪሚየር ደምበኞች አገልግሎት ማናጀር አሚና ነጋሽ ገልጸዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በሕብረቱ ጉባኤ ለመሳተፍ ለመጡ እንግዶች በቀጥታ አገልግሎት የሚሰጡ ጥቅሎችና ሲምካርዶችን አዘጋጅቷል ብለዋል።

እነዚህ አገልግሎቶች የአለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ጥሪ፣ ኢንተርኔትና አጭር የጽሑፍ መልዕክትን ያካተቱ ናቸው ያሉት ሃላፊዋ አገልግሎቶቹ ለሕብረቱ ተሳታፊዎች በዶላር በዮሮና ድርሀም  የቀረቡ ናቸው ሲሉ አስታውቀዋል።

የሞባይል ሽያጭና የይሙሉ ካርድ አገልግሎትም እየተሰጠ እንደሚገኝ አንስተው አገልግሎቱን ኢትዮጵያዊያን  የጉባኤው ተሳታፊዎች ጭምር በመግዛት እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

አገልግሎቱ ጉባኤው ከተጠናቀቀ በሗላ በኢትዮጵያ ለተወሰነ ጊዜ ለሚቆዮ እንግዶች እንደሚያገለግልም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮ ቴሌኮም በጉባኤው የኢንተርኔትና አጠቃላይ የኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ የተሳለጠ እንዲሆን ባለሙያዎችን አሰማርቶ በልዮ ሁኔታ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም