"የሂስ ባህል መጎልበት ለኪነ-ጥበብ እድገት መድሃኒት ነው"

96

ጥር 26/2014/ኢዜአ/ "የሂስ ባህል መጎልበት ለኪነ-ጥበብ እድገት መድሃኒት ነው" ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ የባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሠርፀ ፍሬስብሐት ተናገሩ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ "ብሔራዊ ስሜት በሙዚቃችን የረጅም ዘመን ልምምድ" በሚል መሪ ኃሳብ ያዘጋጀው የኪነ-ሂስ መድረክ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ዛሬ ተካሄዷል።

በአዲስ አበባ ከተማ የባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሠርፀ ፍሬስብሐት በዚህን ወቅት በኪነ-ጥበብ ሥራዎች ላይ ሂስ የመስጠትና ውይይት የማድረግ ባህል አለመዳበሩን ተናግረዋል፡፡

ኪነ-ጥበባዊ ሂስን ከነቀፋ ወይም ከውዳሴ ጋር ብቻ የማያያዝ ልምድ መኖሩን ገልጸው፤ የሂስ ባህል መጎልበት ለኪነ ጥበብ እድገት መድሃኒት ነው ብለዋል፡፡

የሂስ ባህል እንዲጎለብት ደግሞ መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ሚና አላቸው ነው ያሉት፡፡

ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ ከተማ የባህል፣ ኪነጥበባት ቱሪዝም ቢሮ በተለያዩ የኪነ-ጥበብና የሥነ-ጥበብ ስራዎች ላይ የሂስ መድረኮችን ሲያዘጋጅ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

የዛሬው የኪነ-ሂስ መድረክም ለኪነጥበብ እድገት ሚናው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሥነ-ጥበባት ኮሌጅ ዲን የሆኑት ዶክተር ዕዝራ አባተ ሙዚቃ ብሔራዊ ስሜትን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በአንድ የሙዚቃ አልበም ስብስብ ውስጥ አገርን የተመለከቱ ሙዚቃዎች እንዲካተቱ ሲደረግ እንደነበር አስታውሰው፤ በእነዚህ ወቅት የተሰሩ ሙዚቃዎች ዘመናትን ተሻግረው አሁንም የአገር ፍቅር ስሜትን እያነቃቁ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

የሙዚቃዎቹ ግጥም እና ስልተምት ተዋህደው የአገር ፍቅር ስሜትን የገለፁበት መንገድ ኢትጵያውያንን ወደ አንድ ሀሳብ በማምጣት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸው አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበራት ኅብረት ፕሬዘዳንት ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ በበኩላቸው በሙዚቃ ብሔራዊ ስሜትን መፍጠር የሚቻለው በነጻነትና ሙያውን አክብሮ በመስራት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ዘመን ተሻግረው የአገር ፍቅር ስሜትን መቀስቀስ የሚችሉ ሙዚቃዎችን ማበርከት ይቻላል ነው ያሉት፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አዘጋጅነት አምስት የኪነ-ሂስ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን፤ መድረኮቹም በዋናነት በሥነ-ጽሑፍ፣ በሥነ-ሥዕል፣ በፊልምና በቴአትር ዘርፍ ላይ ያተኮሩ እንደነበር ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም