ዳያስፖራዎች በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

65

ደሴ ጥር 26/2014(ኢዜአ) የውጫሌና አካባቢው ተወላጅ ዳያስፖራዎች በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ጉዳት ለደረሰባቸው የውጫሌ ከተማ ነዋሪዎች ከ700 ሺህ ብር በላይ የዓይነትና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አደረጉ፡፡

ዳያስፖራዎቹ  በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖችና ተቋማት መልሶ ለማቋቋም ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ድጋፉ አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት  ምክንያት ለተጎዱ፣ ለአቅመ ደካሞችና ችግር ላጋጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የተበረከተ መሆኑ በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል፡፡

የአይነት ደጋፉ 65 ኩንታል የዳቦ ዱቄትና የትምህርት ቁሳቁስ ያካተተ ሲሆን ለአቅመ ደካሞች ደግሞ በጥሬ ገንዘብ 75 ሺህ ተበርክቷል ።

ዳያስፖራዎቹ በተጨማሪም በአሸባሪው ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን ንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት በ150 ሺህ ብር ወጪ በማስጠገን ለአገልግሎት ማብቃታቸው ተመካክቷል ።

በውጫሌ ከተማ ነዋሪና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ተስፋሁን ይመር በሰጠው አስተያየት በአሸባሪው ቡድን በተተኮሰ ጥይት አንድ እጁን ተመቶ መቁሰሉን ተናግሯል።

በጉዳቱ ሳቢያ አቅመ ደካማ ቤተሰቦቹን በትርፍ ሰዓቱ እየሰራ ለመርዳት የሚያደርገው ጥረት እንቅፋት እንደገጠመው ተናግሯል።

አሁን ላይ የአካባቢያቸው ተወላጅ ዳያስፖራዎች የሚያስፈልገውን የጽህፈት መሣሪያዎች ስላሟሉለት  ትምህርቱን እንደሚቀጥል ገልጻል ።

የተማሪው ወላጅ እናት ወይዘሮ ረህመት አዲስ በበኩላቸው ለልጃቸው የተደረገው የጽህፈት መሣሪያዎች ድጋፍ ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

የአምባሰል ወረዳ አስተዳደር ተወካይ አቶ በቀለ አማረ ዳያስፖራዎቹ   ያደረጉት ድጋፉ  በጦርነቱ ችግር ውስጥ ለወደቁና ልጆቻቸውን ማስተማር ላልቻሉ ወላጆች  እንዲዳረስ መደረጉን ገልጸዋል።

በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ተወካይ አቶ አሰፋ መኮንን  በቀጣይም ከመንግሥት ጎን በመሆን በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለማቋቋምና የፈረሱ ተቋማትን ለመገንባት ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም