የጌዴኦ ብሔር የቋንቋና ባህል ሲምፖዚየም በዲላ ከተማ ጀመረ

73

ዲላ፤ ጥር 26/2014 (ኢዜአ) የጌዴኦ ብሔር የቋንቋና ባህል ሲምፖዚየም በዲላ ከተማ መካሄድ ጀመረ ።

በሲምፖዚየሙ በብሔሩ ባህልና ቋንቋ ዙሪያ ያተኮሩ ከስድስት በላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመጡ ምሁራን ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

የብሔሩን ባህልና ወግ በሲፖዚዬሙ ለማንጸባረቅ ከተደረጉት ዝግጅቶች መካከል የምግብና የአልባሳት ኤግዚብሽን ይገኙባቸዋል።

ይኸው ለ11ኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የቋንቋና ባህል ሲምፖዚየም በዞኑ ላለፉት 20 ቀናት በተለያዩ ወረዳዎች ሲከበር የቆየውና ከነገ በስትያ በዞን የሚከበረው የጌዴኦ ብሔር ዘመን መለወጫ የዳራሮ በዓል አካል ሲሆን ነገ  እንደሚጠናቀቅም ተመላክቷል።  

የዳራሮ በዓል የጌዴኦ ብሔር ዘመን መለወጫ ከመሆኑ ባሻገር የጌዴኦ ሕዝብ ዓመቱን በሰላም ላሻገረ ፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት፣ ለአባገዳ ስጦታ የሚሰጥበት የአንድነትና የፍቅር በዓል ነው።

በሲምፖዚየሙ የፌዴራል፣ የክልልና የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች፤ የጌዴኦ ብሔር ባህላዊ አስተዳደር የ“ባሌ” ስርዓት መሪዎች፤ የኃይማኖት አባቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎች፤ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራንና ተጋባዥ እንግዶች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም