ብሄራዊ የምክክር መድረኩ ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲኖራቸው እድል ይፈጥራል

89

ሆሳዕና፣ ጥር 25/2014 (ኢዜአ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ሊደረግ የታሰበው ብሄራዊ የምክክር መድረክ ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች የጋራ አቋምና ዘላቂ መግባባት እንዲኖራቸው የሚያስችል እድል ይፈጥራል ሲሉ የሀዲያ ዞን ሃይማኖት አባቶች አመለከቱ ።

"የታሰበው ምክክር በየማህበረሰቡና ሃይማኖቱ ያሉ የሰላምና የዕርቅ ዕሴቶችን ታሳቢ ማድረግ አለበት" ሲሉ የሀይማኖት አባቶቹ ጠቁመዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተከርስቲያን የሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መላከ ህይወት ቀሲስ ንጉሴ ባወቀ በሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ እየታየ ያለው የተስፋ ፍንጣቂን ከግብ ለማድረስ ዘላቂ ሰላም መገንባት ወሳኝ ነው።

በተለይም ዜጎች በሀገር ጉዳይ ላይ የጋራ አቋምና መግባባት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል ።

ለዚህ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሊካሄድ የታሰበው የምክክር መድረክ ለልዩነት መነሻ የሆኑ ምክንያቶች በማጥራት ከመሰረቱ የሚቀረፍበት ሊሆን እንደሚችል ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ምክክሩ ለዘላቂ መግባባት መሰረት በመጣል ዜጎች በጋራ የሀገሪቱን ብልጽግናና እድገት ለማረጋገጥ የጀመሩትን ጥረት የሚያጠናክር አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል።

የዞኑ የሀይማኖት ተቋማት ፎረም ዋና ፀሀፊ ኡስታዝ ፃዲቅ ወጌቦ በበኩላቸው "ምክክሩ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ በእኩል የመደመጥና የመወሰን መብታቸውን የሚያስከብር ነው" ብለዋል።

"በየዘመናቱ የተፈጠሩና እየተደራረቡ የመጡ የተለያዩ ቁርሾዎች በዜጎች መካከል በቀላሉ የቅሬታና የግጭት መንስኤ መሆናቸው በኢትዮጵያ የታየ ነው" ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ማዕከላዊ ደቡብ ሲኖዶስ የወንጌል ዘርፍ ኃላፊ ቄስ አለማየሁ ዶለሶ ናቸው።

"የታሰበው ምክክር በየማህበረሰቡና ሃይማኖቱ ያሉ የሰላምና የዕርቅ ዕሴቶችን ታሳቢ ማድረግ አለበት" ያሉት ቄስ አለማየሁ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተፈጠሩ በደሎች ዳግም እንዳይታሰቡ በዘላቂነት ለመፍታት ወሳኝ ድርሻ እንደሚጫወት አመልክተዋል።

"ኢትዮጵያዊያን በየአከባቢው ዕሴት የይቅርታን ታላቅነት ይረዳሉ" ያሉት አስተያየት ሰጪው ዜጎች ይህንኑ በመረዳት ውድቀታችንን ለሚሹ ለውስጥና ለውጭ ኃይሎች ተፅእኖ እድል ባለመስጠት የሀገሪቱን መጻዒ ዕድል የተሻለ ለማድረግ በጋራ መትጋት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም