ቤተክርስቲያኗ 23 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የምግብ እህል እና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገች

67

ደብረ ብርሃን፣  ጥር 25/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን የልማት ኮሚሽን አሸባሪው ህወሓት በለኮሰው ጦርነት በመንዝ ጌራ ወረዳ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች 23 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የምግብ እህልና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገች።

ቤተክርስቲያኗ ዛሬ ድጋፉን ያደረገችው ከኮፓሽን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በወረዳው መሀል ሜዳ ከተማ ነው።

የኢትዮጵያ ቃለሕይወት ቤተክርስቲያን ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ተፈራ ታሎሬ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ወሮ በቆየባቸው ጊዜያት ሰብዓዊነት የጎደለው ግፍ ፈፅሟል።

በወረዳው የተቸገሩ ወገኖችን ለማገዝ ዛሬ ባደረጉት ድጋፍም 3ሺህ 444 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ 344 ኩንታል ጥራጥሬ እና 11 ሺህ 479 ሊትር የምግብ ዘይት እንደሚገኝበት ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለህፃናትና ለነፍሰ ጡር እናቶች 27 ኩንታል አልሚ ምግብ እና ሌሎች የግል ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በድጋፉ ተካተዋል።

ዶክተር ተፈራ እንዳሉት በድጋፍ 23 ሺህ የሚጠጉ ቤተሰቦች ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን የተደረገው ድጋፍም በአጠቃላይ 23 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ነው።

በደቡብ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች ለመልሶ ማቋቋም ሥራ እንዲውልና ለቀጣይ ሁለት ዓመት 113 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ከዚህ ወር አጋማሽ ጀምሮ ወደ እንቅስቃሴ መገባቱንም ተናግረዋል።

የኮፓሽን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የሰሜንና ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የአጋርነት ሥራ አስኪያጅ አቶ አስናቀ ከበደ እንዳሉት ድጋፉ በሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ የተቸገሩ ወገኖችን ሕይወት ለመታደግ የተደረገ ነው።

መደጋገፍ ካለ ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያልፍ ጠቁመው፤ ለሀገር ዕድገት፣ ሰላምና አንድነትም ተባብሮ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከዕለት ደራሽ የምግብ ድጋፍ ባለፈ የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ

እንዲሆኑ 100 የሕክምና ባለሙያዎችን የያዘ ቡድን ተሰማርቶ የስነልቦና ምክርና ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የመንዝ ጌራ ወረዳና አካባቢው ህዝብ በጦርነቱ ምክንያት ለከፋ ችግር መዳረጉን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀይሌ የሺጥላ ገልጸዋል።

"የተደረገው ድጋፍ ማህበረሰቡ ከዕለት ደራሽ ምግብ እሳቤ ባለፈ ወደ ቀደመ ሥራው እንዲመለስ የሚያግዝ ነው" ብለዋል።

በጦርነቱ የወድሙ ተቋማትን መልሶ ሥራ ለማስጀመር እየተደረገ ላለው ጥረት ባለድርሻ አካላትና ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የመሃል ሜዳ ከተማ ነዋሪ ዋና ሳጅን ታለው እንግዳሰው በበኩላቸው አሸባሪው በአካባቢው በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት ተቋማትንና ከቄያቸው የሸሹ ግለሰቦችን ቤት መዝረፉን ተናግረዋል።

"ድጋፉ ችግራችንን ለመፍታትና ወደግል ሥራችን በመግባት በዘላቂነት ለመቋቋም መንገድ ይከፍትልናል" ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን የልማት ኮሚሽን ቀደም ሲል በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ድጋፍ ማድረጓን ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም