ዩኒቨርሲቲው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ውሳኔዎችን በምርምር ለመደገፍ እንደሚሰራ ገለጸ

89

ደብረብርሃን፣  ጥር 25 /2014 (ኢዜአ) የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በስርዓተ ምግብ ማሻሻል ላይ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች በጥናትና ምርምር በመደገፍ ለመተግበር ዝግጁ መሆኑን ደብረብርሀን ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር ገዛኸኝ ደግፌ ለኢዜአ እንደገለጹት የአፍሪካ ህብረት  የመሪዎች ጉባኤ በስርዓተ ምግብ ላይ ለመምከር አጀንዳ መያዙ ወቅታዊና አስፈላጊ ነው።

የአህጉሪቱን ሉአላዊነትና አንድነት ለማረጋገጥ የአፍሪካ ሀገራትን የምግባ ዋስትና ማረጋገጥና የስርዓተ ምግብ ማሻሻል ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመፍታትና የስርዓተ ምግብን ለማሻሻል አገር በቀል ኢኮኖሚ ልማት መርሃ ግብር በመንደፍ እየተሰራ እንደሚገኝ ዶክተር ገዛኸኝ አውስተዋል።

መረሀ ግብሩ የምግብ ይዘትን በሳይንሳዊ ዘዴና በምርምር ማሻሻል ፤ የምግብ ሰብሎችን ምርታማነት ማሳደግ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲውም ድርቅን የሚቋቋሙና በተለያዩ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ   እንደ አደንጓሬ፣  እንሰትና ሌሎች ተክሎችንና ሰብሎችን ወደ አካባቢው በማምጣት እያላመደ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በተጨማሪም በዶሮና በአሳ እርባታ፣ በተፈጥሮ ማዳበሪያና ሌሎች ተያያዥ ዘርፎች ጥናትና ምርምር በማካሄድ በሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች የምግብ ክፍተትን ለመሙላት እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል ።

35ኛው የአፍረካ ህብረት ጉባኤ የሚያስተላልፋቸውን የስርዓተ ምግብ ማሻሻያ ውሳኔዎች በምርምር በማዳበር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚሰሩ ተግባራት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የኤክስቴሽን ኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ አቶ ታለ ለማ በበኩላቸው የህብረቱ አጀንዳ  የገጠርና የከተማን ነዋሪ መሰረት ያደረገ የስርዓተ ምግብ ለመተግበር የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

 "አጀንዳው በዞኑ የሚገኙ 26ሺህ 214 እናቶች የስብጥር አመራረትን በመከተል በጓሮአቸው አትክልትና ፍራፍሬ፣ የስራስር፣ የጥራጥሬ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ የወተት ተዋጽኦ እንዲያመርቱ እየተደረገ  ያለውን ተግባር ያጠናክራል" ብለዋል።

የአፍሪካ መሪዎች የሚያስተላልፉትን ውሳኔ መሰረት ያደረገ ስራ ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም