በአማራና አፋር ክልሎች በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ኤሌክትሪክ የተቋረጠባቸው ከተሞች አገልግሎቱን አገኙ

62

ደሴ፣ ጥር 25/2014(ኢዜአ) በአማራና አፋር ክልሎች በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ኤሌክትሪክ የተቋረጠባቸው ከተሞች አገልግሎቱን መልሰው ማግኘታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ በደቡብ ወሎ ዞን በአሸባሪው ቡድን ወረራ ለተጎዱ ዜጎች ከ1ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ እህል፣ ቁሳቁስና አልባሳት ድጋፍ አድርጓል፡፡

የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመዝረፍና በማውደም ለሕዝብ ያለውን ጥላቻ በተግባር አሳይቷል፡፡

"ቡድኑ የሕዝብ መገልገያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መሠረተ ልማትን አውድሞ ሕዝቡን ለጨለማ ከመዳረጉም ባለፈ የቻለውን ዘርፎ፣ ያልቻለውን ዳግም አገልግሎት እንዳይሰጥ አድርጓል" ብለዋል።

ቡድኑ በአማራ ክልል በሁለት ዲስትሪክቶችና በ30 ማዕከላት፣ በአፋር ደግሞ በስድስት ማዕከላት እንዲሁም በኮምቦልቻ የግብዓቶች ማስቀመጫ መጋዘን የነበረ ትራንስፎርመሮችን ጨምሮ ሙሉ ንብረት መዝረፉን ተናግረዋል።

"ይሁን እንጂ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በተደረገ ጥረት ከተሞቹ ከአሸባሪው ቡድን ነጻ በወጡ ማግስት ጀምሮ መሥመሮች በመዘርጋትና በመጠገን በአጭር ጊዜ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል"  ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ በቡድኑ ወረራ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍና የወደሙ ተቋማትን መልሶ በማደራጀት ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ድጋፉ ከዋና መሥሪያ ቤቱ አመራሮችና ሠራተኞች መሰባሰቡን አስታውቀዋል።

ከድጋፉ የዳቦ ዱቄት፣ የምግብ ማብሰያ ቁሳቁስ፣ ንጽህና መጠበቂያዎች፣ አልባሳትና ጫማ ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው  በተለይም መልሶ ለማደራጀትና ለማቋቋም ትኩረት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል ።

የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ማሩ ተቋሙ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ አገልግሎቱ የመልሶ ማቋቋሙን ሂደት ለመደገፍ ያሳየው ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

መንግሥት ተቋማትንና ህብረተሰቡን በማስተባበር የዕለት ደራሽ ምግብ ለማቅረብ ጥረት እያደረገ ቢሆንም፤ ከችግሩ ስፋት አንጻር በቂ ባለመሆኑ ድጋፉ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም