ተለዋጭ መንገድ በመበላሸቱ ከአዲስ አበባ ፣ ውጫሌ ደሴ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ተስተጓጎለ

133

ደሴ፤ ጥር 25/2014 (ኢዜአ)፡ በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ውጫሌ ከተማ መግቢያ አሸባሪው ህወሃት በድልድይ ላይ ያደረሰውን ውድመት ተከትሎ የተሰራ ተለዋጭ መንገድ በመበላሸቱ ከአዲስ አበባ ፣ ውጫሌ ደሴ የሚደረግ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ በመስተጓጎሉ መቸገራቸውን ተሳፋሪዎችና አሽከርካሪዎች ገለጹ።

በመንገዱ ብልሽት  ከዛሬ ጧት ጀምሮ በርካታ ተሽከርካሪዎች በመቆማቸው መንገደኞች እየተጉላሉ መሆኑ ተመላክቷል።

ከአሽከርካሪዎች መካከል አቶ ሰለሞን አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ተለዋጭ መንገዱ ጠባብ በመሆኑ በተደጋጋሚ ለብልሽት ይዳረጋል።

ዛሬ  መንገዱ ሙሉ በሙሉ በመዘጋቱ  ለአስቸኳይ ስራ ከውጫሌ ወደ ደሴ መድረስ ቢፈልጉም እንዳልቻሉ ጠቁመው የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

መንገዱን በማስተካከል ለመክፈት የትራፊክ ፖሊሶችና ባለድርሻ አካላት ጥረት እያደረጉ መሆኑን መመልከታቸውን ያስረዱት አሽከርካሪው ለመንገዱ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠቁመዋል።

ከተሳፋሪዎች መካከል  አቶ ይከበር አለሙ በበኩላቸው ለአስቸኳይ ስራ ከደሴ ወደ ውጫሌ እየተጓዙ ቢሆንም በመንገድ መዘጋት መጉላላታቸውን ተናግረዋል።

መንገዱ  አማራጭ መንገድ የሌለው መሆኑን ጠቁመው  የሚመለከተው አካል በአፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮምቦልቻ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሳምሶን ተስፋዬ ከወልዲያ ደሴና ከደሴ ወልዲያ በሚወስደው መንገድ ውጫሌ ከተማ መግቢያ የሚገኘው ድልድይ አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈፀመበት ወቅት መሰበሩን አስታውሰዋል።  

ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት በተለዋጭ መንገድ የትራንስፖርት አገልግሎቱ እንዲቀጥል መደረጉን አመልክተዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ  ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተሰበረው ድልድይ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ዛሬ በመንገድ ብልሽት የተከሰተውን የመንገድ መዘጋት በፍጥነት በመፍታት ለተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ክፍት እንደሚደረግ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም