ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ዕድገት የድርሻውን እየተወጣ ነው

79

ባህርዳር ጥር 25/2014 (ኢዜአ) የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በዕውቀት ላይ ለተመሰረተ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው የጨርቃ ጨርቅና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከ106 ሚሊዮን ብር በላይ ያስገነባው ዘመናዊና ሁለገብ የቤተ-መጻሕፍት ሕንጻ ተመርቋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ተልዕኮን በአግባቡ ለመወጣት እየሰራ ነው።

ሀገሪቱ በምታስመዘግበው ሁለንተናዊ ዕድገት ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በዕውቀትና ክህሎት አሰልጥኖ በማውጣት የልማቱ አካል እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ የሚካሄደው የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ዘርፎች ዕድገት እንዲያመጣ ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዕድገታችን የራሳችንን ባህል፣ ጥበብና ዕውቀታችንን መሰረት ያደረገ እንዲሆን እንደ ጨርቃጨርቅና ፋሽን ቴክኖሎጂ ያሉ ተቋማት ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸው አስረድተዋል።

ቤተ-መጻሕፍቱ ሳቢ፣ ውብና ማራኪ ሆኖ መገንባቱ የተቋሙ ተማሪዎች፣ የአካባቢው ማህበረሰብና ተመራማሪዎች እየተዝናኑ ዕውቀትን እንዲጨብጡ የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል።

"የአካባቢውን ማህበረሰብ ኃብትና ዕውቀት ለማሳደግ የፋሽንና ዲዛይን ቱሪዝምን ማስፋፋት ተገቢ ነው" ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ናቸው።

የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የማህበረሰብ እውቀትን ወደ ፊት ለማሸጋገር የቤተ-መጻሕፍት ተደራሽነትን ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም በማንበብ፣ በጥናትና ምርምር በማካሄድ መጽሐፎችን በመጻፍ የመጪውን ትውልድ በዕውቀትና ክህሎት ለማነጽ ተግቶ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ተቋሙ ያስመረቀው ቤተ-መፃህፍትም ከመደበኛ ተግባሩ በተጨማሪ የክልሉን ቅርስና ዩኒቨርሲቲውን ማስታወሻ የሚቀመጥበት ሙዚየም ሆኖ የሚያገለግል ነው ብለዋል።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የጨርቃ ጨርቅና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ታምራት ተስፋዬ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ በሀገር ደረጃ የመጀመሪያ በመሆኑ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ነው የጠቀሱት።

ለዚህም 19 የትምህርት ፕሮግራሞችን በመክፈት በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች ተማሪዎችን ተቀብሎ በማሰልጠን የጨርቃ ጨርቅና ፋሽን ዘርፉን እየደገፈ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የሚያሰለጥናቸው ተማሪዎች ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት ጨብጠው እንዲወጡም ዘመናዊ ቤተ-መፃህፍት በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች እገዛ ተገንብቶ ለምረቃ መብቃቱን ተናግረዋል።

ቤተ-መጻሕፍቱ የማህበረሰብ፣ የተማሪዎችና የዲጅታል ቤተ-መፃህፍትን አካቶ የተገነባ ሲሆን ቤተ መዘክር፣ ግሪን ላይብረሪና ካፊቴሪያ እንዳለው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም