የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የህብረቱን የመሪዎች ጉባኤ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የአፍሪካን መልካም ገፅታ ለዓለም ማስተዋወቅ አለባቸው

59

ጥር 25/2014 የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የህብረቱን የመሪዎች ጉባኤ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የአፍሪካን መልካም ገፅታ ለዓለም ማስተዋወቅ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ገለጸ።

35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የፊታችን ቅዳሜና እሁድ የሚካሄድ ሲሆን 40ኛው የህብረቱ ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ደግሞ ዛሬና ነገ ይካሄዳል።

ጉባኤውም “የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፣ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ማፋጠን” በሚል መሪ ሃሳብ  ነው የሚካሄደው፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለ ስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሙሃመድ ኢድሪስ፤ የመገናኛ ብዙሃን የጉባኤውን አጠቃላይ ሁኔታ ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ የአፍሪካን መልካም ገፅታ ለዓለም ለማስተዋወቅ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጊዜውን ጠብቆ በአዲስ አበባ መካሄዱ ኢትዮጵያን እውነት ለማሳወቅ ትልቅ እድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል፡፡

የህብረቱን የመሪዎች ጉባኤ ለመዘገብ ከ300 በላይ የሃገር ውስጥ ጋዜጠኞችና ከ200 በላይ የውጭ አገር ጋዜጠኞች የሚገኙ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ጉባኤው የያዛቸውን አጀንዳዎችና ውሳኔዎች ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ትልቅ አቅም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጉባኤውን የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ከመደበኛ ዘገባቸው በተጨማሪ የአፍሪካን መልካም ገፅታ ለዓለም ማሳየት እንደሚጠበቅባቸውም ነው የገለጹት።

ጋዜጠኞቹ ያለ ምንም እንከን ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውንም ተናግረዋል፡፡

የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ከዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋር ትስስራቸውን በማጥበቅና መረጃ በመለዋወጥ የኢትዮጵያን ሰላምና መልካም ገፅታ ማሳወቅ እንደሚጠበቅባቸውም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጉባኤውን ለመዘገብ ለሚመጡ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም