የአፍሪካ ህብረት የአስፈፃሚ ምክር ቤት ጉባኤ ተሳታፊ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ ገብተዋል

71

አዲስ አበባ ጥር 25/2014(ኢዜአ) በ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የአስፈፃሚ ምክር ቤት ተሳታፊ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ ገብተዋል።

በ40ኛው የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ዋና ጸሀፊን ጨምሮ በርካታ የህብረቱ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ ገብተዋል።

የኬኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ማላዊ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ የናሚቢያ፣ የኮሞሮስ፣ የብሩንዲና የሞዛምቢክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል።

ሌሎች በርካታ አፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቀደም ብለው አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የኬኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ረሺያ ኦማሞ፣ የዩጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኦሪም ሄነሪ ኦክሎ፣ የማላዊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናይሲ ቴምቦ፣ የኢኳቶሪያል ጊኒ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሜን ኦዩኖ ኢሶኖ፣ የኮሞሮስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሂር ዶልካማል፣ የብሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር አልብረት ሺኒጊሮ፣ የሞዛንቢክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቬሮኒካ ማካሞ ዛሬ በሚጀመረው የአስፈፃሚ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል።

የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ዋና ጸሐፊ ቻሊሻ ኩማፑአ በህብረቱ ጉባኤ ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ ተገኝተዋል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የካቤኔ ጉዳዮች ዋና ሹም አምባሳደር ምህረትአብ ሙሉጌታ፤ በጉባኤው የሚሳተፉ በርካታ የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ መግባታቸውን ገልጸዋል።

የሰሜን አፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም በኩዌት ሲካሄድ የነበረውን የአረብ ሊግ ስብሰባ አጠናቀው አዲስ አበባ በመግባት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ሕብረት 40ኛው የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባኤ ዛሬ የሚጀምር ሲሆን በሕብረቱ አባል አገራት የጋራ ፍላጎት የሆኑ የፖሊሲ ጉዳዮችን የሚያስተባብርና ውሳኔ የሚሰጥ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም