መዋእለ ንዋያቸው ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሆኑ የቻይና ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ሥራ ላይ ይገኛሉ

56
አዲስ አበባ ነሀሴ 24/2010 በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ መዋእለ ንዋያቸው ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሆኑ የቻይና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የልማት መስኮች ተሰማርተው እንደሚገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። እነዚህ በቁጥር አራት መቶ የሚሆኑት የቻይና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች  ከመቶ ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል የፈጠሩ መሆናቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። ከኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ መካከል ከ105 በላይ የሚሆኑት በኢትዮጵያውያንና ቻይናውያን ባለሃብቶች ጥምረት የተቋቋሙ ናቸው። አገራቱ ወጥ የሆነ ተከታታይ እድገት እያሳየ የሚገኝ የላቀ የመሰረተ-ልማት፣ የፋይናንስና ንግድ ትብብር መመስረታቸውም ተገልጿል። ይህን ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ከማጠናከር አንፃር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአገራችን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ደረጃ 10 የስራ ጉብኝቶችን በቻይና በማካሄድ ከአገሪቱ ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር ሰፊ ውይይቶች ተደርገዋል። ስለአገራችን የቱሪዝም ሃብቶች እና በአገራችን ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች በስፋት የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱንም የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጨምሮ ጠቁሟል። ከ50 በላይ ግዙፍ የቻይና ኩባንያዎች በቅርቡ በኢትዮጵያ የቻይና ንግድ ሳምንት ጉባኤ በማካሄድ ከኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ አቻዎቻቸው ጋር አብሮ መስራት የሚያስችል ትስስር እንዲፈጥሩ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውም ተነግሯል። በሁለቱ አገራት መካከል በተደረሰው የስትራቴጂካዊ ትብብር ስምምነት መሰረት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማስፋት ሰፊ የማግባባት ስራ ተከናውኗል። የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት አንዳለው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሌሎች ስልጠናዎችን ሳይጨምር ከሁለት ሺ በላይ  ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ነፃ የማስተርስና ዶክትሬት ትምህርት እድል ከቻይና አግኝተዋል። ኢትዮጵያና ቻይና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን፣ የደቡብ-ደቡብ እና የቻይና አፍሪካ ትብብር መድረኮችን ጨምሮ በተለያዩ የባለብዙ ወገን ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላቸው የትብብርና የመደጋገፍ ባህልም በተመሳሳይ ጠንካራ ነው። ኢትዮጵያና ቻይና በተለያዩ መስኮች ያላቸ ግንኙነት ወጥና ተገማች በመሆኑ የደቡብ-ደቡብ ትብብር ጽንሰ-ሃሳብ ውጤታማነት ማሳያ ነው። ይህን ትብብር ለማጠናከር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የሚሳተፉበት የቻይና አፍሪካ  የትብብር መድረክ ስብሰባ ከነሐሴ 28-29 ቀን 2010 ዓ.ም. በቻይና ቤጂንግ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም