አሸባሪው ህወሃት በአማራ እና አፋር ክልሎች እያደረሰ ባለው አዲስ ጥቃት የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ላይ እክል እየፈጠረ ነው - አቶ ደመቀ መኮንን

51

ጥር 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) በመንግስት በኩል ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ ቁርጠኝነት ያለ ቢሆንም የህወሃት የሽብር ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች እያደረሰ ባለው አዲስ ጥቃት ምክንያት እክል እየፈጠረ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የፈረንሳይን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛን አምባሳደር ፍሬድሪክ ክላቬዬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን የፈረንሳይና እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ መሆኑን አስታውሰው፤ በቀጣይ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት መኖሩን አስረድተዋል፡፡

የፈረንሳይ መንግስት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ሚዛናው በሆነ መልኩ መመልከቱም የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሁኔታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ መምጣታቸውን፣ መንግስት ለሰላም ሲል በቅርቡ እስረኞችን መፍታቱን፣ ብሔራዊ መግባባትን ያለመ ሁሉን አቀፍ ውይይት ለማድረግ እየተሰራበት መሆኑን፣ እንዲሁም በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት እና ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በመንግስት በኩል ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ ቁርጠኝነት ያለ ቢሆንም የህወሃት የሽብር ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች እያደረሰ ባለው አዲስ ጥቃት ምክንያት እክል እየፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የፈረንሳይ ልዩ መልዕክተኛው አምባሳደር ፍሬድሪክ ክላቬዬ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ማብራሪያና ገለጻ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ኢትየጵያ በአካባቢው ጠንካራ እና ተጽእኖ ፈጣሪ አገር መሆኗን ጠቅሰው፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለመጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የኢትየጵያ መንግስት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ለሚያደርገውን ጥረት የፈረንሳይ መንግስት እንደሚደግፍ ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ ለሚደረገው ውይይትም መንግስታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ልዩ መልዕክተኛው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም