በባሌ ዞን ከ140 ሺህ ኩንታል በላይ የቡና ምርት ተሰበሰበ

263

ጎባ ጥር 24/2014 (ኢዜአ) --- በባሌ ዞን በመኽር የምርት ወቅት በቡና ተክል ከለማው መሬት ከ140 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ከተሰበሰበው የቡና ምርት መካከል እስከ አሁን 40ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡም ተመልክቷል።

በልማቱ የተሳተፉ የደሎ መና አርሶ አደሮች ቡናን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል የዕውቅና ምስክር ወረቀት ያገኙ አርሶ አደሮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹ እንዳሉት ይህም ለቡና  ምርታማነት ሰፊ የገበያ አማራጭ እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።

በጽህፈት ቤቱ የቡና ልማት፣ ጥራትና ቅመማ ቅመም ቡድን መሪ አቶ ወንደሰን ነጋ ለኢዜአ እንደገለጹት ምርቱ የተሰበሰበው  በዞኑ  በቡና ልማት ከተሸፈነው 53 ሺህ  ሄክታር መሬት ነው።

ከዞኑ ስምንት ቡና አብቃይ ወረዳዎች ውስጥ ከተሰበሰበው የቡና ምርት መካከል እስከ አሁን 40 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ  ቡና  ለማዕከላዊ  ገበያ መቅረቡን አመልክተዋል፡፡

ለማዕከላዊ ገበያ የቀረበው ቡና ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ35 በመቶ ብልጫ እንዳለው ባለሙያው ተናግረዋል።

የቡድን መሪው እንዳሉት በዞኑ ለማዕከላዊ ገበያ የቀረበው የቡና ምርት ብልጫ ሊያሳይ  የቻለው የቡና  ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ  መሻሻል ማሳያቱን በምክንያትነት  አስቀምጠዋል።

እንዲሁም በግለሰብና በማህበር  ተደራጅተው ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡ የአምራች ላኪነት የምስክር ወረቀት ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ያገኙ አርሶ አደሮች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ዘንድሮ ለቡና ልማት ጥራት በተሰጠው ትኩረት ምክንያት ቀይ  ቡና  ተለቅሞ የሚደርቅበት ከ526 ሺህ ሜትር እስኩዬር በላይ የሽቦ አልጋ በመንግሥትና በልማት ድርጅቶች ለአርሶ አደሩ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

በዞኑ በቡና ተክል ከለማው 53 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 24 ሺህ 300 የሚበልጡ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች እየተሳተፉ ናቸው።

በኦሮሚያ ክልል የግብርና ቢሮ  ምክትል  ኃላፊና  የቡናና  ፍራፍሬ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ መሐመድሳኒ አሚን እንዳሉት ዘንድሮ ከ9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

ምርቱን ለመሰብሰብ የተወጠነው በክልሉ የቡና አብቃይ በሆኑ 18  ዞኖች በቡና ተክል ከተሸፈነው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን  ሄክታር መሬት መሆኑንምተናግረዋል።

አስተባባሪው እንዳሉት  እስከ አሁን እንደ የዞኖቹ የስነ-ምህዳር ሁኔታ ከተሰበሰበው የቡና መሬት 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መቻሉን አመልክተዋል።

 በክልሉ ከሚሰበሰበው የቡና ምርት መካከል 50 በመቶ የሚሆነው ለገበያ እንዲቀርብ በቡና ጥራትና ህገወጥ የቡና ንግድ እንቅስቃሴን በመከላከልና በመቆጣጣር ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በክልሉ ቡናን ለዓለም አቀፍ ገበያ እንዲያቀርቡ የዕውቅና ምስክር ወረቀት ያገኙ አርሶ አደሮች ቁጥር 600 መድረሳቸውን አስረድተዋል።

ይህም ለቡና ጥራት የተሰጠው ትኩረት ለገበያ ለማቅረብ የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካ በማገዝ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳበረከተም ጠቁመዋል፡፡

በደሎ መና ወረዳ በልማቱ ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል ሼህ ሙስጠፋ አማን በሰጡት አስተያየት በቡና ልማት የመሳተፍ የቆየ ልምድ ቢኖራቸውም ከገበያ እጦት የተነሳ የልፋታቸውን ያክል ተጠቃሚ እንዳልነበሩ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢያችን ቡናን እስከ ዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ ፈቃድ ያገኙ አርሶ አደሮች ቁጥር እየጨመረ መምጣት ሰፊ የገበያ አማራጭ እንዲያገኙ እንደረዳቸውም ተናግረዋል።

ቡናችን ከሀገር ውስጥ ገበያ አልፎ በዓለም ገበያም ተፈላጊ እንዲሆን ለቡና ጥራት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን በወረዳው የልማቱ ተሳታፊ  አርሶ አደር አህመድ ከድር ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በቡና ተክል የተሸፈነ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥም 59 በመቶ የሚሆነው ምርት የሚሰጥ መሆኑን ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም