የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ደህንነት፣ ጥራትና አስተማማኝነት የሚያስጠብቅ ፖሊሲ እየተዘጋጀ ነው

108

አዳማ፣ ጥር 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ደህንነት፣ ጥራትና አስተማማኝነት የሚያስጠብቅ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ፖሊሲውን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ለማሰባሰብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ እየመከረ የሚገኘው ሚኒስቴሩ፤ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት አሰጣጥን ደህንነት፣ ጥራትና አስተማማኝነት ለማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ገልጿል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ የሳይበር ደህንነት ሥራ አመራርን ለመተግበር ራሱን የቻለ ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

እየተዘጋጀ ያለው የፖሊሲ ረቂቅ ፖሊሲው የሳይበር ሥራ አመራርን በአግባቡ ለመምራት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

የሳይበር ጥቃት መነሻ ኢንዱስትሪዎችና መንግሥታዊ ተቋማት መሆናቸውን ጥናቶች እንደሚያመላክቱ ገልጸው፤ 92 በመቶ የሚሆኑት የሳይበር ጥቃቶች የሚፈፀሙት በኢሜይል ልውውጥ እንደሆነ አመልክተዋል።

ፖሊሲው የሚዘጋጀው ሁሉም መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች የሚመሩበት ፖሊሲ በማስፈለጉ እንደሆነም አስረድተዋል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል ጋር እየተዘጋጀ ያለው ፖሊሲ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከልና ከተከሰተም ሊኖር የሚችለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ፖሊሲ፣ አሰራሮችና የሕግ ማዕቀፎች እንዲኖሩ ለማገዝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመንግሥት መረጃ ደህንነት ማስጠበቂያ ፖሊሲ በማዘጋጀት በሁሉም መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግ፣ አሰራሮችና ማዕቀፎችን ለመምራትና ለመቆጣጠር እንደሚያስችል  አመልክተዋል።

የሳይበር ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና መምጣቱን ያነሱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር መሥፍን ክፍሌ፤ "ችግሩን ለመከላከል ራሱን የቻለ አሰራር፣ የሕግ ማዕቀፎችና ፖሊሲዎች ያስፈልጓታል" ብለዋል።

ረቂቅ ፖሊሲው ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም ወሳኝ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር መሥፍን፤ "በተለይ መፍትሄዎች ለማፈላለግና አቅጣጫዎችን ለማስቀጠል ያስችላል" ብለዋል።

በየጊዜው መልካቸውን የሚቀያይሩ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል፣ ስጋትና ተጋላጭነትን ለመቀነስ፣ የሚፈጠሩ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋምና ዓለም አቀፍ ባህሪያትን የዳሰሰ ፖሊሲ ለማዘጋጀት ረቅቅ ፖሊሲው መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

በረቅቅ ሰነዱ ዝግጅቱ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች፣ የደቡብ ኮሪያ፣ የማሌዥያና የኢንዶኔዥያ የሳይበር ደህንነት ተሞክሮዎችና ልምዶች መካተታቸውን ዶክተር መሥፍን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም