በቄለምና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እየተሰጠ ነው

86

ጊምቢ ጥር 24/2014/( ኢዜአ)- በቄለምና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች በፀጥታ ችግር ምክንያት ተራዝሞ የነበረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ዛሬ መሰጠት መጀመሩን የዞኖቹ ትምህርት ጽህፈት ቤቶች አስታወቁ።

በቄለም ወለጋ ዞን በ12 ወረዳዎችና በምዕራብ ወለጋ ዞን በቤጊና ቆንዳላ ወረዳዎች ከ15ሺህ በላይ ተማሪዎች ፈተናውን በመውሰድ ላይ መሆናቸውን ጽህፈት ቤቶቹ ለኢዜአ አስታውቀዋል።

ፈተናው ዛሬን ጨምሮ ለአራት ቀን እንደሚሰጥ አመልክተዋል።

የቄለም ወለጋ ዞን የትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ምክትል  ሃላፊ አቶ ኤፍሬም ተፈራ እንደገለጹት በዞኑ በ12 ወረዳዎች በ42 የፈተና ጣቢያዎች ለ14ሺህ 228 ተማሪዎች ፈተናው እየተሰጠ ይገኛል።

ፈተናውን ይወስዳሉ ተብለው ከሚጠበቁት 16ሺህ 608 ውስጥ 1ሺህ 243 ተማሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ለፈተናው እንዳልተቀመጡ ገልጸዋል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን የትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዮናስ እምሩ በበኩላቸው የቤጊና ቆንዳላ ወረዳዎች የሚገኙ 1ሺህ137 ተማሪዎች በመንዲ ከተማ  በተዘጋጁ አራት ጣቢያዎች ፈተናውን እየወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ፈተናውን እየወሰዱ ካሉ ተማሪዎች መካከል 118ቱ የግል ተፈታኞች መሆናቸውን አመልክተዋል ።

"በተለያዩ ምክንያቶች 931 ተማሪዎች ለፈተና መቀመጥ አልቻሉም" ብለዋል፡፡

ፈተናው በሁለቱም ዞኖች ያለምንም የፀጥታ ችግር እየተሰጠ መሆኑን ሃላፊዎቹ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም