የ6ኛው ዙር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሴቶች ኮከስ ተመሰረተ

171

አዲስ አበባ ጥር 24/2014(ኢዜአ) የ6ኛው ዙር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሴቶች ኮከስ ተመሰረተ።

የምክር ቤት አባላት የሴቶች ኮከስ የመመስረቻ ጉባኤውን በዛሬው እለት አካሒዷል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ፤ የሴት ምክር ቤት አባላት ኮከስ በ2ኛው የምክር ቤት ዘመን የተመሰረተ አደረጃጀት መሆኑን ገልጸዋል።

ኮከሱ አዲስ ምክር ቤት ሲቋቋም አብሮ የሚመሰረት በመሆኑ የ6ኛው ዙር ሴት የምክር ቤት አባላት የሴቶች ኮከስ መመስረቱን ተናግረዋል።

ኮከሱ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ፣ መብትና ጥቅም በማስከበር ረገድ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል።

በምክር ቤቱ የሚፀድቁ አዋጆች፣ አገራዊ እቅዶች እና አለም አቀፍ ስምምነቶች የሴቶችን ህገ-መንግስታዊ መብቶች የሚያስጠብቁ መሆናቸውን የማረጋገጥ ስራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰዋል።

May be an image of 2 people, people sitting and people standing

በተለይም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማጠናከር ረገድ የተለያዩ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።

የሴቶች ኮከስ ባለፉት ሶስት አመታት በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች እና በተፈጥሮ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ በማሰባሰብ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ሲወጣ እንደቆየም ጠቁመዋል።

በመሆኑም የ6ኛው ዙር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሴቶች ኮከስ ምስረታ እውን መሆኑ የተጀመሩ መልካም ተሞክሮዎችን በማስቀጠል ለሴቶች ተጠቃሚነት ይበልጥ ለመስራት ያግዛል ብለዋል።

በየደረጃው እስከ ቀበሌ በሚደርሱ መዋቅሮች ኮከሱን በማደራጀት ውጤታማ ስራ እንደሚከናወን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በተለይም በገጠር አካባቢ ያሉ ሴቶችን የኑሮ ጫና ሊቀንሱ የሚችሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እገዛ ያላቸውን ተግባራት የማከናወን እቅድ እንዳለ ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ወይዘሮ ቁስቋም ማሞ፤ ኮከሱ በተለይም ለሴቶች መብት መከበርና ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የሴቶችን ክህሎትና አቅም የመገንባት፣ የውሳኔ ሰጭነት ሚናቸውን የማሳደግ፣ የክትትል እና ድጋፍ ስራዎችም የቀጣይ ትኩረት ይሆናሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም