በትውልደ ኢትዮጵያዊው ያዴሳ ቦጂያ የተዘጋጀው የአፍሪካ ህብረት ሰንደቅዓላማ

67

አፍካውያን በፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ወቅት ፖለቲካዊ ነፃነትና ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለመቀዳጀት በርካታ ተጋድሎ አድርገዋል።

አፍሪካዊቷ ኢትዮጵያ የተጓዘችበትን የአይበገሬነት የትግል መርህ በመከተልም በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ ሀገራት  ቅኝ አገዛዝን አስወግደዋል፤ የነፃነት ትግሎችን ለማቀጣጠል ፓን አፍሪካኒዝም በመላው አፍሪካና በጥቁር ህዝቦች ዘንድ እንዲቀጣጠልም አድርገዋል።

የፓን አፍሪካኒዝም ትግሉ ተጠናክሮ አህጉራዊ ፖለቲካዊ አንድነትን ግቡ ያደረገ ድርጅት (የአፍሪካ አንድነት ድርጅት) በኢትዮጵያና ሌሎች አፍሪካውያን ሀገሮች በፈረንጆቹ 1963 አዲስ አበባ ለይ ተመስርቷል።

ይህ ድርጅት አፍሪካዊ አንድነትን ለማጎልበት እስከ ፈረንጆቹ 2002 ድረስ የዘለቀ የዘመናት ትግልን ያደረገ ሲሆን በኋላም በአፍሪካ ህብረት ተተክቷል።

የአፍሪካ ህብረትም ከፈረንጆቹ 2002 ጀምሮ የአፍሪካ ድምጽ፣ የመሰባሰቢያቸው አዳራሽ፣ የመመካከሪያቸው መንበር፣ ሆኖ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል። 

ህብረቱ ስራ በጀመረበት ዓመት የራሱ ሰንደቅዓላማ ያልነበረው ህብረቱ በ2004 ግን መለያ ሰንደቅዓላማ አዘጋጅቷል።

ሆኖም ስምንተኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በፈረንጆቹ ጥር 29 እና 30 ቀን 2007 በአዲስ አበባ ሲካሄድ ነባሩን ሰንደቅዓላማ የሚተካ አዲስ የህብረቱ ሰንደቅዓላማ እንዲዘጋጅ ውሳኔ አሳልፎ ነበር።

በወቅቱ የሊቢያ መሪና የህብረቱ ሊቀመንበር ሙአመር ጋዳፊ የሚመራው የአፍሪካ ህበረት ኮሚሽንም ኃላፊነቱን ወስዶ ለህብረቱ ሰንደቅዓላማ ንድፍ መስራት ለሚፈልጉ ጥሪ አቀረበ፤ የኮሚሽኑን ጥሪ ተከትሎም ከ19 የአፍሪካ ሀገራት ከ100 በላይ ግለሰቦች፣ ከዳያስፖራ ሁለት ግለሰቦች ከ100 በላይ ንድፎችን አስገቡ።

የሰንደቅዓላማ ንድፎቹ በባለሙያዎች ተመዝነው  አሸናፊው ሲለይ ትውልደ ኢትዮጵያዊው በዜግነት አሜሪካዊ የሆነው የግራፊክ ጠቢብ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ያዴሳ ቦጂያ ያቀረበው ንድፍ አሸናፊ ሆነ።

ያሸነፈው የያዴሳ ንድፍም ሰንደቅዓላማ እንዲሆን በፈረንጆቹ ጥር 31 ቀን 2010 በአዲስ አበባ በተካሄደው 14ኛው መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተወሰነ።

ያዴሳ ቦጂያ ያረቀቀውና አሁን በስራ ላይ ያለው የህብረቱ ሰንደቅዓላማ አረንጓዴ መደብ፣ በ55 ወርቃማ ኮከቦች የተከበበችና በነጭ የፀሐይ ጨረሮች ላይ ያረፈች አረንጓዴ የአፍሪካ ካርታን የያዘ ነው።

የአፍሪካ ካርታ በአረንጓዴ መወከሉ አህጉራዊ ተስፋን ለማሳየት ሲሆን፣ ነጭ የፀሐይ ጨረሮች ደግሞ አፍሪካውያንን ከተቀረው ዓለም ጋር በወዳጅነት፣ በጋራ የመኖር ግልፅ ፍላጎትን የሚያሳይ ነው።

አረንጓዴው የአፍሪካ ካርታ በ55 ወርቃማ ኮከቦች የተከበበ ሲሆን ተምሳሌትነቱ 55ቱን የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራትን፥ የአፍሪካን ፀጋዎችና ብሩህ ተስፋን የሚያሳይ ነው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም