አዲሱ ትውልድ በንባብ የዳበረ ዕውቀት እንዲኖረው ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ መጻህፍት ማስፋፋት ይገባል

80

ባህር ዳር ኢዜአ 24/2014(ኢዜአ) አዲሱ ትውልድ በንባብ የዳበረ ዕውቀት እንዲኖረው ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ መጻህፍት ማስፋፋት እንደሚገባ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አመለከቱ።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከ106 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባው ዘመናዊ ሁለገብ ቤተ መጻህፍት ዛሬ ተመርቋል።

ቤተ መጻህፍቱ  በዩኒቨርሲቲው ሥር ለተቋቋመው ለኢትዮጵያ ቴክስታይል፣ ፋሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት አገልግሎት እንደሚሰጥ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂር  ስለሺ በቀለ በምረቃው ላይ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

በሥሩ የተቋቋመው ኢትዮጵያ ቴክስታይል፣ ፋሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም በአገሪቱ የአልባሳትና ዲዛይን ዘርፍ የመጀመሪያው የእውቀት መገበያያ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

ለኢንስቲትዩቱ የተገነባው ቤተ-መጻህፍት ወጣቱን ትውልድ በእውቀት ላይ የተመሰረተና አገር ወዳድ አድርጎ ለማውጣት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ትውልዱን ከማህበራዊ ሚዲያ ጥገኝነት ደረጃ በደረጃ በማላቀቅ በንባብ የዳበረ እውቀትና ክህሎት ለመጨበጥ እንደሚረዳው  አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ሌሎች የትምህርት ክፍሎችንም ለማስፋፋት መሰል ቤተ መጻህፍትን እንዲከፍቱም አሳስበዋል።

የተቋሙ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ታምራት ተስፋዬ በበኩላቸው  ቤተ-መጻህፍቱ የህፃናት፣ የሴቶች፣ የቅድመና ድህረ ምረቃ ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ክፍሎች እንዳሉት አመልክተዋል።

በተጨማሪም የማንበቢያ ሰገነት፣ የማንበቢያ አረንጓዴ ስፍራና ካፍቴሪያ፣ሙዚዬምና ዲጂታል- ቤተ

መጻህፍትን አካቶ የያዘ እንደሆነም አስታውቀዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ "ቤተ-መጻህፍቱ በፋሽንና ዲዛይን ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል በማፍራት በተለይ የባህር ዳርን የቱሪዝም ዘርፍ የሚያሳልጡ ባለሙያዎችን ለማፍራት  እገዛ ያደርጋል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም