ሀገራዊ ለውጡ በዕድገትና ብልጽግና ታጅቦ እንዲቀጥል በተባበረ መንፈስ መትጋት ያስፈልጋል-ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

63

ሚዛን ጥር 24/2014 (ኢዜአ) ሀገራዊ ለውጡ በዕድገትና በብልጽግና ታጅቦ የዜጎችን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ በመትጋት ሊሆን ይገባል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አስገነዘቡ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሀገራዊና ክልላዊ ወቅታዊ ጉዳዮች እንዲሁም የልማት ፕሮጄክቶች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በወቅቱ እንደተናገሩት ሀገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብቶችና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ተጠቅማ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የለውጥ ጉዞ ከጀመረች ሶስት ዓመት ተቆጥሯል።

በፖለቲካ ሸፍጥ ምክንያት ሳይመለሱና ለዘመናት በቅሬታ የቆዩ የመዋቅር ጥያቄዎችን ጨምሮ በርካታ የተረሱ አከባቢዎች በሰፋፊ የልማት ስራዎች እንዲተሳሰሩ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

"ሀገራዊ ለውጡ በታለመው ልክ ዘርፈ ብዙ በሆነ ዕድገትና ብልጽግና ታጅቦ የዜጎችን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ከግብ እንዲደርስ የሁሉም የተባበረ ትጋት ይፈልጋል" ብለዋል ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ “ሁሉም እኔ ማለትን በመተው እኛ በሚል መንፈስ ለጋራ ዕድገት ከተጋ ሀገራዊ ለውጡ ዕውን የማይሆንበት ምክንያት የለም" ብለዋል።

በተለይ ክልሉ ያሉትን የተፈጥሮ ፀጋዎች የኛ ብሎ በጋራ አልምቶ መጠቀም ከቻለ ወደ ዕድገት ማማ ቶሎ መድረስ እንደሚችል አመላክተዋል።

ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል በመፍጠርና አንድነትን በብዝሃነት ውስጥ በማጠናከር ለሁለንተናዊ ለውጥ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።


በህዝብ ዘንድ ቅሬታ ሲፈጥሩ የቆዩ ተጀምረው ያልተጠናቀቁና የተጓተቱ የቦንጋ ንጹህ መጠጥ ውሃ ፣ የቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዚየምና መሰል ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው የታለመላቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

"የህዝብ የጎለበተ አንድነት ከምንም የላቀ ሀብት ነው" ያሉት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ ናቸው።

"ያለንን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ እየተጠቀምን ጠንካራ አንድነት ካጎለበትንና አንድ ሆነን ከሰራን የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ የጋራ ተጠቃሚነታችን ፍሬ በማፍራት ወደ ብልጽግና ለመሸጋገር ድልድይ ይሆነናል" ብለዋል።

"በተለይም አለመግባባቶችን በመነጋገር፣ ችግሮችን በመደጋገፍ፣ ልማትን በትብብር በማከናወን ቱባ ዕሴቶቻችንን ልናጎለብት ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል።

እንደ ክልል ያሉ መልካም አጋጣሚዎችንም ሆነ ክፍተቶችን የኛ ናቸው በማለት ተቀብሎ መስራት ከአመራር ጀምሮ በሁሉም ህብረተሰብ ውስጥ መስረጽ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የካፋ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ "ክልሉ ራሱን ችሎ ከተደራጀ በኋላ የህዝብን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የጀመረው ጥረት የሚያስደስት ነው" ብለዋል።

ዞኑ ከክልሉ መንግስት ጋር በቅርበት እየተደጋገፈ ህብረተሰቡን በሚገባ ለማገልገል ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ማማሩ በላይ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት በቅርበት የህዝቦችን ችግር ለመረዳትና ለመፍታት መሞከሩ  በህዝብና በመንግስት መካከል መተማመንን ይበልጥ የሚያጎለብት መሆኑን አመልክተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም