አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት በመሪዎቹ ጉባኤ ላይ ጠንካራ አቋም መያዝ አለበት

132

 ጥር 24 ቀን 2014 (ኢዜአ)  አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት በመሪዎቹ ጉባኤ ላይ ጠንካራ አቋም መያዝ እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ተናገሩ።

የዓለም የፀጥታ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮች ውሳኔ በሚተላለፍበት በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።

በመሆኑም የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ጠንካራ አቋም መያዝ እንዳለበት በርካቶች ይገልፃሉ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ የሚሉትም ይህንኑ ነው።

አፍሪካ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ህዝብ እየኖረባት በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ወኪል እንዳይኖራት መደረጉ በየትኛውም መመዘኛ ትክክል አለመሆኑን ይናገራሉ።

በጥቂት ኃያላን ፍላጎት ላይ ተመስርቶ የሚዘወረውን የዓለም ፖለቲካ ፈር ለማስያዝ አፍሪካ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል ይላሉ።

በመሆኑም በፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት በመሪዎቹ ጉባኤ ላይ ጠንካራ አቋም ሊያዝ ይገባል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የነበረውን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት በነበረው ጥረት በርካታ አፍሪካውያን ከጎኗ መሰለፋቸውን አስታውሰው የአፍሪካን ችግር አፍሪካዊያን መፍታት እንደሚችሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የገጠሟትን ፈተናዎች አልፋ የመሪዎችን ጉባኤ ማስተናገድ መቻሏም የዲፕሎማሲ ድል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በፀረ ቅኝ አገዛዝ ዘመን ከሌሎች አፍሪካዊያን ጋር በትብብር ታግላ ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት የላቀ ሚና እንደነበራት ይታወቃል።

በመሆኑም በቀጣይ በአህጉሩ ጉዳዮች ላይ የመሪነት ሚናዋን ማጠናከር እንዲሁም ውስጣዊ ችግሮቿን በመፍታት ለሌሎችም አርአያ ሆና መቀጠል አለባት ብለዋል።

35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ “የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፤ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ያፋጥናል” በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም