አመራሩ የተሰጠውን ዕድል ተጠቅሞ አገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ የማሻገር ተልዕኮውን ሊወጣ ይገባል- -- አቶ ርስቱ ይርዳው

70

ሃዋሳ፣ ጥር 24/2014(ኢዜአ) በየደረጃው ያለው አመራር ህዝቡ በምርጫ የሰጠውን እድል ተጠቅሞ አገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ የማሻገር ተልዕኮውን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ፡፡

"መመረጥ ተለውጦ አገርን ለመለወጥ" የሚል መርህን የያዘ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የውይይት መድረክ ዛሬ በሃዋሳ ከተማ ተጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ርስቱ ይርዳው በውይይቱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት ብልጽግና በህዝብ ድምጽ የተመረጠ ፓርቲ መሆኑን አስታውሰው፣ ፓርቲው ህዝቡ የሰጠውን አደራ በብቃት እንዲወጣ የሚመጥን ብቁ አመራር ሊኖር ያስፈልጋል።

በየደረጃው ያለ አመራር ህዝቡ በምርጫ የሰጠውን ዕድል ተጠቅሞ አገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ የማሻገር ተልዕኮውን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"በመድረኩ አመራሩ ህዝቡ የሰጠውን ዕድል ተጠቅሞ አገራዊ ለውጡን ከመምራት አኳያ ያስመዘገባቸውን ድሎችና ድክመቶች ይፈትሻል" ያሉት አቶ ርስቱ፣ ካለፉት ትውልዶች እየተሸጋገረ የመጣውን የፖለቲካ አስተሳሰብ መቀየር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

"አገሪቱ በድህነት እንድትታወቅ ያደረጋት የፖለቲካው አለመዘመን በመሆኑ ከችግሩ ለመውጣት ወደ ሰለጠነ የአመራር ብቃት መድረስ ያስፈልጋል" ብለዋል።

በፍቅርና በይቅርታ በመሻገር አንድነትን ማጠናከርና ለሁሉ የምትበቃ አገር መፍጠር እንደሚያስፈልግ ነው አቶ ርስቱ ያስረዱት።

በጦርነት፣ በግጭት፣ በመጠፋፋት፣ አንዱ ሌላውን በማሳደድ ኢትዮጵያ ትውልዶቿን እያጣች በመሆኑ ብልጽግና ፓርቲ ይህንን ታሪክ ለመቀየር እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ርዕስ መስተዳድሩ እንዳሉት ብልፅግና በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሻገር ራዕይ አንግቦ እየሰራ ነው።

በመሆኑም በየደረጃው ያለው አመራር የዜጎችን አቅምና እውቀት ተጠቅሞ አገርን የማሻገር ሃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ አሳስበዋል።

ባለፉት ዓመታት ፓርቲው እንደአገር ብዙ ፈተናዎች ማለፉን አቶ ርስቱ አስታውሰው፣ እንደ ክልል በተለያዩ አካባቢዎችም የተከሰቱ ግጭቶች ፓርቲው ተልዕኮውን በአግባቡ እንዳይወጣ መሰናክል ሆነው ማለፋቸውን አመልክተዋል።

"በችግሮቹ የተፈተነው የክልሉ አመራር በቀጣይ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በመመለስ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ይሰራል" ብለዋል።

የአመራሩን ውስጣዊ ሁኔታዎች በመፈተሸ በቅርቡ ለሚደረገው የፓርቲው ጉባኤ የጠራ አመራር ይዞ ለመሄድ ጠቀሜታ እንዳለው ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

ለሦስት ቀን በሚቆየው የውይይት መድረክ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶችና ጉድለቶች በዝርዝር ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም