ማህበሩ ሀገር በቀል ዕውቀቶችንና ማህበረሰባዊ እሴቶችን ጠብቆ በማቆየት ትውልድን የማስተሳሰር አስተዋጾው የላቀ ነው

84

እንጅባራ፣ ጥር 24/2014 ( ኢዜአ) የአገው ፈረሰኞች ማህበር ሀገር በቀል እውቀቶችንና ያልተበረዙ ማህበረሰባዊ እሴቶችን ጠብቆ በማቆየት ትውልድን በማስተሳሰርና ታሪክን ለበጎ ተግባር ለመጠቀም እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን የታሪክና ቅርስ ምሁራን አመለከቱ።

የማህበሩ 82ኛ አመት ምስረታ በአል አስመልክቶ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አለማየሁ እርቅይሁን ለኢዜአ እንደገለጹት ማህበሩ የአድዋ ጀግኖች ለሀገር የከፈሉትን መስዋዕትነት ለማሳየት የተመሠረተ ቢሆንም ሀገር በቀል ዕውቀት፣ ማንነትንና ትውፊት ሳይበረዝ ለትውልድ ለማሻገር እያገለገለ ነው።

ማህበሩ ግጭትን ከማስወገድ አኳያ ባለው አወቃቀር፣ በባህልና በወግ መሰረት  አባላቱን በመምከር ትናንሽ ልዩነቶች እንዳይሰፉ በማድረግ  ሰላምን የሚያስጠብቅ የሀገር በቀል ዕውቀት ባለቤት መሆኑን ተናግረዋል ።

ማህበሩ የማህበረሰቡ መልካም እሴቶች የሚንጸባረቁበት፣ የማንነት መገለጫ እሴቶችን ጠብቆ በማቆየት የትውልድ ትስስር በመፍጠር አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል ።

ማህበሩም ሆነ የማህበሩ ባህላዊ እሴቶች  እንዲጠበቅና እንዲተዋወቁ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የክልሉና የፌደራል የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

"ማህበሩ ሴቶችንና ወንዶችን ፤ ፈረስ ያለውን ከሌለው ጋር አካትቶ  የያዘና አወቃቀሩ ከቀበሌ እስከ ዞን መዘርጋቱ ዲሞክራሲያዊነቱን ያሳያል "ብለዋል።

የማህበሩ በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ለጅምሩ ስኬት ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ  አመልክተዋል።

''ኢትዮጵያ በአባቶች ተጋድሎ የነጻነት ታሪክ ያላት ቢሆንም በመጤ ልማድ እንዳይበረዝ ሊጠበቅ ይገባል'' ያሉት ደግሞ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና አስተዳደር ምሁር ረዳት ፕሮፌሰር አለሙ አለነ ናቸው።

ማህበሩ ያልተበረዘ ባህልንና ታሪክን ከፈረስ ጋር ባለው የጀግንነት ታሪካዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር በማሻገር ሚናውን በራሱ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

"ማህበሩ ባለው አደረጃጀትና መዋቅር፣ በማይጣስ መተዳደሪያና የስልጣን ቆይታ አማካኝነት ያልተበረዘ የአባቶችን ዴሞክራሲያዊ ሂደት ለትውልድ ለማስረከብ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል "ብለዋል።

"ህገ ወጥነትን የሚጠላና አጥፊን ከማንኛውም ማህበራዊ ተሳትፎዎች በማገድ እንዲታረም ከማድረግ ባለፈ በእርቅና የተበደለ እንዲካስ በማድረግ ለህግ የበላይነት መከበር ሚናውን እየተወጣ ይገኛል" ብለዋል።

"ምሁራን በየዓመቱ ጥር 23 በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ያለውን  በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ በእውቀት ላይ ተመስርቶ በማስተዋወቅ የቱሪስት መስህብ እንዲሆን መስራት ይገባናል " ሲሉ አክለዋል።

የማህበሩን ምስረታና በዓል በየዓመቱ ከማክበር ባለፈ ለትውልድ ለማሸጋገርና የበለጠ ለማልማት የፈረስ ጉግስ ልምምድ ሜዳ፣ እርባታና አመጋገብ ላይ ማተኮር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ማህበሩ 59 ሺህ አባላት ያሉት ሲሆን ከዞን እስከ ቀበሌ የራሱ አለቃ፣ አጋፋሪ፣ ፀሃፊና ሂሳብ ሹም የተሰኙ መዋቅሮችን የያዘና በየደረጃው ከ6 ሺህ በላይ አመራሮች ያሉት ስለመሆኑ ታውቋል።

እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የማህበሩን ታሪካዊ አመሰራረት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ጫና የተመለከተን ጨምሮ በዓሉን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ጥናታዊ ጽሁፎች በምሁራን ቀርበዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም