የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፈው ዓመት ከ3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ገለጸ

179

ጋምቤላ፣ ጥር 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር ደንበኞችን ወደ ለውጥ መስመር በማስገባቱ ባለው ዓመት ከ3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።

በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶችን በመደገፍ በዘርፉ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በጋምቤላ ክልል በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተሰማሩ ደንበኞቹ ጋር ውይይት ያካሄደው ባንኩ፤ የተሰራጩ ብድሮች በሚመለሱበትና በኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ባለሃብቶችን መደገፍ በሚቻልባቸው ሁኔታ ላይ መክሯል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው በውይይት መድረኩ ላይ እንዳሉት፤ በግብርና ዘርፍ ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ባንኩ የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችን በማስተካከል በዘመናዊ የእርሻ ልማት ለተሰማሩ ባለሃብቶች የብድር አገልግሎትና ሌሎች ድጋፎችን ለመስጠት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

“ባለፈው ዓመት 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ነው ያተረፍነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የባንኩ ትርፍ ታክስን ጨምሮ 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሆኑን ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል 154 የእርሻ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም ቀደም ሲል በነበረው የብድር አሰጣጥ ክፍተት 62ቱ ብቻ በስራ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች ተገቢ ባልሆነ መልኩ ወጪ የሆኑ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ለማስመለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክትር ተገኝወርቅ ጌጡ በበኩላቸው ባንኩ ግብርና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በሆነው በዘመናዊ የእርሻ ልማት ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊውን የብድር አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ ዝናብ ላይ ብቻ የተመሰረተና ዘመናዊ የግብርና አሰራር ዘይቤ ለማይከተሉ ባለሃብቶች የብድር አገልግሎት ቦርዱ መከልከሉን ጠቁመው፤ ባንኩ ክልከላውን ያደረገው ባለፉት ዓመታት ከሰጠው ብድር ውስጥ 7 ቢሊዮን ብር በመታጣቱ መሆኑን አመልክተዋል።

በውይይቱ ላይ ከተሳተፉ ባለሃብቶች መካከል አቶ ዳዊት መላኩና አቶ እየሩስ ዓለም በሰጡት አስተያየት “ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ ከነበረው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ባንኩ የወለድ ምጣኔና የብድር መክፈያ ጊዜን ሊያሻሽል ይገባል” ሲሉ  ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼