የአፍሪካን እውነታ ለዓለም ሕዝብ የሚያስገነዝቡ ዘገባዎችን ለመስራት ተዘጋጅተናል

73

ጥር 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የአፍሪካን እውነታ ለዓለም ሕዝብ የሚያስገነዝቡ ዘገባዎችን ለመስራት መዘጋጀታቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ መንግስት የሕብረቱ መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ይካሄድ ዘንድ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ ይገኛል።

ከዝግጅቶቹ መካከል አንዱ 35ኛ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የኮቪድ 19 ወረርሺኝን መከላከል በሚያስችል መልኩ መካሄድ እንዲችል ነው።

ለዚህም የሕብረቱን ጉባኤ የሚዘግቡ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሙያተኞች የኮቪድ-19 ምርመራ አድርገዋል።

በህብረቱ ጉባኤ ላይ በዘገባ ስራ ከሚሳተፉት መካከል ኢዜአ ያነገጋራቸው ባለሙያዎች የሙያ ስነ-ምግባሩ በሚፈቅደው መልኩ ለጉባኤው የዘገባ ሽፋን ለመስጠት ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

35ኛ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ከቀደሙት ጉባኤዎች ከሚለዩት ምክንያቶች መካከል ከኮቪድ-19 ወረርሺኝ መከሰት በኋላ የሕብረቱ አባል አገራት መሪዎች በአካል ተገናኝተው ሲመክሩ የመጀመሪያ መሆኑ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ የተለያዩ ጫናዎች ቢደረጉም የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነታ በመረዳት መሪዎቹ በአዲስ አበባ ተገናኝተው ለመምከር መወሰናቸው ነው።

በመሆኑም በዚህ የተለየ ጉባኤ መላው ዓለም የአፍሪካን ትክክለኛ እውነታ የሚያውቅበት መልካም አጋጣሚ በመሆኑ የተረጋገጡ ዘገባዎችን ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል ጋዜጠኞቹ።

የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ጋዜጠኛ አስታርቃቸው ወልዴ፤ ለአፍሪካ ነፃነትና አንድነት እውን መሆን የጎላ ድርሻ የነበራቸውን አገራት አስተዋጽኦ በዘገባችን ማሳየት ይገባናል ብሏል።

የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ ጋዜጠኛ በላይ ተሰማ፤ የአፍሪካዊያንን አንድነት እና ትብብር በትክክል የሚያሳይ ዘገባ ለመስራት ዝግጁነቱን ገልጿል።

ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያ ጫና ውስጥ በገባችበት ወቅት አፍሪካውያን ያሳዩትን አለኝታነት በዘገባችን ለማሳየት መስራት አለብን ብሏል።

''አፍሪካዊያን ተባብረው በመቆም ያገኙትን ድል የሚያንጸባረቁ ዘገባዎችን እንሰራለን'' ያለው ደግሞ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋዜጠኛ ብስራት መለሰ ነው።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ ተስፋዬ ጫኔ በበኩሉ ዘገባ ከመስራት ባለፈ ለሚመጡት እንግዶች በአካል ቀርቦ የኢትዮጵያን እውነታ ማሳወቅም ይገባል ይላል።

35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የፊታችን ቅዳሜና እሁድ የሚካሄድ ሲሆን 40ኛው የህብረቱ ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ቀደም ብሎ ረቡዕ እና ሐሙስ ይካሄዳል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም