የቼክ ሪፐብሊክ ጎብኚዎች በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ፍፁም ሰላም መሆኑን ተናገሩ

124

ጥር 23 ቀን 2014 (ኢዜአ)የቼክ ሪፐብሊክ ጎብኚዎች በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ፍፁም ሰላም መሆኑንና ምንም አይነት የደኅንነት ሥጋት እንዳላጋጠማቸው ተናገሩ።

አስራ አምስት የቼክ ሪፐብሊክ ጎብኚዎችን የያዘ ቡድን የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሥጦታ የሆኑትን የአዕዋፍ ዝርያ በመጎብኘት ላይ ይገኛል።

ቡድኑ ለአንድ ወር በኢትዮጵያ በሚኖረው ቆይታ በአእዋፍ ዝርያና ባህሪ ላይ ጥናት የሚያደርግ ሲሆን ይህንንም የሚያከናውኑ የዘርፉ ባለሙያዎችን ይዞ መጥቷል።

እስካሁንም ቡድኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ የተመረጡ አዕዋፋት መገኛ ሥፍራዎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

ጉብኝቱን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ ያሉትን በርካታ ድንቅ የአዕዋፍ ዝርያዎች ለመጎብኘት መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ከጎብኚዎቹ መካከል ሚሮስላቭ ቻፔክ፤ ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ሕዝቡ እንግዳ ተቀባይ ከመሆኑ ባሻገር ኢትዮጵያ የበርካታ አዕዋፋት መገኛ በመሆኗ ነው ብሏል።

ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የወሰንነው ኢትዮጵያ በርካታ የአዕዋፍ በተለይም የብርቅዬ አእዋፍ ዝርያዎች መገኛ መሆኗ ነው ያለው ደግሞ ሌላኛው ጎብኚ ሉካስ ቪክቶራ ነው።

በሌላ በኩል ቡድኑ ተዘዋውሮ ጉብኝት ባደረገበት አካባቢዎች ፍጹም ሰላማዊ ጉብኝት ማከናወኑንና ምንም አይነት የጸጥታ ስጋት አለመኖሩን ገልጿል።

ከጎብኚዎቹ መካከል ቶማስ ፖጃር፤ አዲስ አበባና ዙሪያን ጨምሮ ተዘዋውሮ በጎበኘባቸው አካባቢዎች ያጋጠመው ምንም አይነት ችግር እንደሌለ አረጋግጧል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ፍፁም ሰላም ነች፤ የኢትዮጵያዊያን እንግዳ አቀባበልም አስደናቂ በመሆኑ ሁላችሁም መጥታችሁ ጎብኙ ሲል መልእክቱን አስተላልፏል።

በአዲስ አበባና ዙሪያዋ እንዲሁም ጉብኝት ባደረጉባቸው አካባቢዎች ሰላም ነው፤እዚህ በመገኘቴም ምቾት ይሰማኛል ብሏል ሉካስ ቪክቶራ።

ሌሎች ጎብኚዎችም የኢትዮጵያን አስደናቂና የማይጠገቡ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ኃብቶች መጥተው እንዲጎበኙ ሚሮስላቭ ቻፔክ ጥሪ አቅርቧል።

ቡድኑ በቀሪዎቹ የጉብኝት ቀናት ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በማቅናት የተለያዩ የአእዋፍ ዝርያዎችን ለመመልከት ተዘጋጅቷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም