ዩ ኤስ ኤድ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ሰብአዊ ድጋፍና የልማት ፕሮግራም አጠናክሮ ይቀጥላል

81

ጥር 23 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት /ዩ ኤስ ኤድ/በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ሰብአዊ ድጋፍና የልማት ፕሮግራም አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የዩ ኤስ ኤድ ዳይሬክተር ገለጹ።

በኢትዮጵያ የድርጅቱ ዳይሬክተር ሲን ጆንስ፤ላለፉት በርካታ ዓመታት ዩ ኤስ ኤድ በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ተኮር የልማት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

በተለይም እናቶችና ህፃናት ሞት ቅነሳ፣በትምህርት፣በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ፣በጤና እና በንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

ድርጅቱ በግብርና፣በምግብ ዋስትና ፕሮግራሞችና በሌሎችም መሰል ሰብአዊ ድጋፎችና የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ ሁነኛ አጋር ሆኖ ሲሰራ ቆይቷል፤አሁንም ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በዚህ ዓመትም በኢትዮጵያ ድርቅ በተከሰተባቸው ደቡብ ኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልል እና በደቡብ ሶማሌ አካባቢዎች ድጋፍ ለማድረግ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በአማራ፣ትግራይ እና አፋር ክልሎች እርዳታ ለሚሹ ሰዎች ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤በልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚኖረውን አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

"አሜሪካ ጠንካራና የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት ትፈልጋለች" ሲሉም ተናግረዋል።

ዩ ኤስ ኤድ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ከሰብአዊ ድጋፎች በተጨማሪ የተለያዩ የልማት ስራዎችን የማከናወን እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በማህበራዊ፣በኢኮኖሚ፣በጤና፣በዴሞክራሲና በሌሎችም መስኮች በትብብር እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በመመደብ ግብርናን በማሻሻል፣የእናቶችና ህጻናትን ጤና በመጠበቅ፣የገበያ ሁኔታን ማሻሻልና ሌሎችም የተፈጥሮ ሃብት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚተገበር ፕሮጀክት በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በዚህ መርሃ ግብርም ከ1 ነጥብ 2 እስከ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ 

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም