በአገራዊ ምክክር መድረኩ ኅብረተሰቡ የተሻለ አመለካከት እንዲይዝ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል

83

ጥር 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአገራዊ ምክክር መድረኩ ኅብረተሰቡ የተሻለ አመለካከት እንዲይዝ መገናኛ ብዙሃን የተዛቡ አመለካከቶችን የሚያጠሩ ስራዎች ተደራሽ በማድረግ ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የሕገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል አስገነዘበ።

ማዕከሉ ኅብረተሰቡ ውይይት በሚሹ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

በሕገ መንግስትና ፌዴራሊዝም ዙሪያ አስተምህሮ በመስጠት ንቃተ ሕገ መንግስቱ ያደገና የፌዴራሊዝም አስተሳሰቡ የዳበረ ኅብረተሰብ የመፍጠር ተልዕኮን ያነገበው ማዕከል በአዋጅ 1123/2011 የተቋቋመ ነው።  

ማዕከሉ በፌዴራሊዝም፣ ሕገ መንግስት፣ ሕገ መንግስታዊነትና የመገናኛ ብዙሃን ሚና ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የሶስት ቀናት የመጀመሪያ ዙር የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ጀምሯል።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኃይለኢየሱስ ታዬ እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ በአገር ውስጥ ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱ ከ200 በላይ መገናኛ ብዙሃን 50 ዎቹን በመምረጥ ባደረገው የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት መሰረት ነው ስልጠናውን መስጠት የጀመረው።

ስልጠናው በቀጣይም በትምህርት ቤቶች፣ በሲቪክ ማኅበራትና በሌሎች ተቋማት ለሚሰሩ ባለሙያዎች እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የማዕከሉ አሰልጣኝ አቶ ኖህ ያደሳ ኅብረተሰቡ ወደ አገራዊ ምክክር ከመግባቱ አስቀድሞ በውይይቱ ሊነሱ በሚችሉ ርዕሰ ጎዳዮች ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በሕገ መንግስት፣ በፌዴራሊዝምና በሕገ መንግስታዊነት ላይ ኅብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ ይዞ ወደ አገራዊ ምክክር እንዲገባ ማድረግ ደግሞ የማዕከሉ ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ማዕከሉ ይህንን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ለማድረግ በተዛቡ አመለካከቶች ላይ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖረው መገናኛ ብዙሃን የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም