የጉጂና ቡርጂ ህዝቦች ወደ ቀድሞ ትስስራቸው ለመመለስ እየተሰራ ነው- የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር

82
ሃዋሳ ነሀሴ 24/2010 በምዕራብ ጉጂ ዞን አዋሳኝ በሆኑ የቡርጂ ወረዳ አካባቢ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቄያቸው ለመመለስና የተዘጉ መንገዶችን ለማስከፈት እየተሰራ መሆኑን የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ። ችግሩን በዘላቂነት መፍታትና ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ  በሚቻልበት ዙሪያ ዛሬ በቡርጂ ሶያማ ውይይት በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በሚኒስቴሩ የግጭት መከላከል ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ደምሴ በውይይቱ ላይ እንዳሉት ለረጅም አመታት በጋራ የሚኖሩትን የጉጂና የቡርጂ ህዝቦች ወደ ቀድሞ ትስስራቸው ለመመለስ እየተሰራ ነው። ''በጌድኦ አካባቢ የተፈናቀሉ አብዛዎቹ ወገኖች ወደ ቄያቸው ተመልሰዋል፤ በቡርጂና አማሮ ወረዳዎች ያሉትን ተፈናቃዮች ደግሞ ለመመለስ ዝግጅቱ ተጠናቋል''ብለዋል። የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳደር አቶ አበራ ቡኖ እንዳሉት የቡርጂና የጉጂ ህዝቦች በጋብቻ የተሳሰሩና የተወራረሰ ባህል ያላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በእነዚህ ህዝቦች መካከል ለተፈጠረው ችግር ምክንያት የሆነውን ጉዳይ የማጥራት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የተባሉ አመራሮችና ግለሰቦችን ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በውይይቱ ላይ የፌዴራል፣ የኦሮሚያ ክልል፣ የጉጂ ዞን እና በደቡብ ክልል የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን አመራሮችና ከቡርጂ ወረዳ 26 ቀበሌዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች  ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ውይይቱ በነገው ዕለትም በአማሮ ወረዳ እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም