የግሸን ደብረ ከርቤ አስተርዮ ማርያም በዓልን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል- ሀገረ ስብከቱ

72

ደሴ፣   ጥር 20/2014 --(ኢዜአ) -አመታዊውን የግሸን ደብረ ከርቤ አስተርዮ ማርያም በዓልን በነገው እለት ሀይማኖታዊ ስርአቱን ጠብቆ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት አስታወቀ።

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ መምህራን ብርሃነህይወት እውነቱ ለኢዜአ እንደገለጹት አመታዊው የግሸን ደብረ ከርቤ በአል በመስከረምና ጥር 21 በድምቀት ይከበራል።

በዚህ አመት አካባቢው በአሸባሪው ህወሀት በወረራ ተይዞ በመቆየቱ የመስከረም 21ዱ በአል ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ይመጡ የነበሩ ጎብዎችና ምእመናን እንቅስቃሴ በመገታቱ እንደወትሮው ሳይከበር ቀርቷል።

ጥር 21 የሚከበረውን የግሸን ደብረ ከርቤ አስተርዮ ማርያም በአልን በነገው እለት በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በአሉን በድምቀትና በሰላም ለማክበር የእንግዶች ማረፊያ፣ የተሸከርካሪ ማቆሚያ፣ የህክምና መስጫና ሌሎች አገልግሎቶች ዝግጁ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል ።

በክብረ በአሉ ላይ ከ1 ሚሊዮን በላይ ምዕመንና ጎብኚዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

የግሸን ደብረ ከርቤ ቤተ ክርስቲያንና ገዳም ዋና አስተዳዳሪ መምህር አባ ለይኩን ወንድይፍራው በበኩላቸው የበዓሉ ታዳሚዎች አቅመ ደካሞችንና አረጋውያንን በማገዝ ትብብር እንዲያደርጉ መልእክት አስተላልፈዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው መንግስት ለቱሪዝም ዘርፍ ልዩ ትኩረት ቢሰጥም በአገራዊና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ምክንያት ዘርፉ መቀዛቀዝ ታይቶበት መቆየቱን ተናግረዋል።

ከኮሮና ቫይረስ መስፋፋትና አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት የተቀዛቀዘው ቱሪዝም እንቅስቃሴ በሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቦታዎች የሚከበሩ በዓላትን በመጠቀም ለማነቃቃት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በየዓመቱ ጥር 21 ቀን በግሸን ደብረ ከርቤ የሚከበረውን የአስተርዕዮ ማርያም በዓል በድምቀትና በሰላም ለማክበር የዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በዓሉን ለመታደም ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚመጡ ምዕመናንና ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ የእንግዳ አቀባበል ባህልና እሴት ተቀብሎ ለማስተናገድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

የፀጥታ መዋቅሩም የአካባቢውን ሰላምና መረጋጋት የሚያጠናክሩ ተግባራትን ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር እያከናወነ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

የዞኑ የባህልና ቱሪዝም መምሪያው ኃላፊ አቶ ሱለይማን እሸቱ በበኩላቸው በዓሉ በሚከበርበት አካባቢ የጤና፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና የሌሎች አገልግሎቶች ችግር እንዳያጋጥም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በትብብር መሰራቱን አመልክተዋል።

በአካባቢው በጦርነቱ የስነ ልቦና ጉዳት የደረሰበት ማህበረሰብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን በዓሉን በድምቀት በማክበር መንፈሱን ማደስ እንዲችል ዝግጅት መደረጉን ኃላፊ አስታውቀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም