ለስራ ፈጠራ ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል

101

ጥር 20/2014(ኢዜአ) የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ለስራ ፈጠራ ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን በማሻሻል ወጣቶች ስራ ፈጣሪነትን ባህል እንዲያደርጉት እንደሚሰራ ገለጸ፡፡

ሚኒስቴሩ በወጣቶች የሥራ እና  ክህሎት ሥነ ባህሪ ላይ ያተኮረ ጥናት ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ሚኒስቴሩ  ጥናቱን ያከናወነው ከዴቪድ እና ሉሲ ፓካርድ ፋውንዴሽን እንዲሁም ቢቢሲ ሚዲያ አክሽን ጋር በጋራ በመሆን ነው፡፡

ጥናቱም ወጣቶችን በማነቃቃት፣ አቅማቸውን በመገንባት እንዲሁም የህይወት እና የሥራ ምርጫቸው የተሻለ እንዲሆን የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን ሥራዎችን በማከናወን ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባ አመላክቷል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን በዚህን ወቅት ሚኒስቴሩ ለስራ ፈጠራ ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን በመፍታት ወጣቶች ስራ ፈጣሪነትን ባህል እንዲያደርጉት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ሚኒስቴሩ በአምስት ዓመቱ ስትራቴጂክ ዕቅዱ ላይ በዘርፉ የሚሆን ብቁ የሰው ሀብት ማፍራት ላይ ትኩረት መስጠቱን አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያሉ አቅሞችን ለስራ ፈጠራ ማዋልም እንዲሁ፡፡

በሥራ ፈጠራው ዘርፍ 44 በመቶ የሚሆነውን ግብርና እንዲሁም 22 በመቶውን ደግሞ ኢንዱስትሪ ድርሻ እንዳላቸውም ነው የገለጹት፡፡

ቀሪው 24 በመቶው የአገልግሎት ዘርፍ እንደሚሸፍነው ጠቅሰው፤ በተለይ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች በአገልግሎት ዘርፍ ብቻ የመሰማራት ዝንባሌ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ይህም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በቀጣይነት ለማሻሻል እንቅፋት እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ሚኒስቴሩ በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚሰማሩ ስራ ፈጣሪዎች ልዩ ድጋፍ በማድረግ ዘርፉን ለማነቃቃት እንደሚሰራ አውስተዋል፡፡

የፓካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ፕሮግራም ኃላፊ ወይዘሮ የምስራች በላይነህ በበኩላቸው፤ እያንዳንዱ የመንግስት ተቋም ለወጣቶች ሥራ መፍጠርን እንደ አንድ ኃላፊነት አድርጎ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ 2 ሚሊዮን ስራ ፈላጊ ወጣቶች ገበያውን እንደሚቀላቀሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም