በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩላችንን ድጋፍ ለማድረግ ፕሮጀክት ቀርጸን እየሰራን ነው

79

አዲስ አበባ፣  ጥር 20/2014(ኢዜአ)  በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩላችንን ድጋፍ ለማድረግ ፕሮጀክት ቀርጸን እየሰራን ነው ሲሉ ከጣልያን የመጡ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ተናገሩ፡፡

አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ሰላማዊ ዜጎችን ከመጨፍጨፍ ባሻገር፤ ሆስፒታሎች፣ የትምህርት ተቋማትና ሌሎችም በርካታ የህዝብ መገልገያዎችን አውድሟል።

አሁን ላይ በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎችና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም መንግስት፣ ኀብረተሰቡና ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ ነው፡፡

ከጣልያን አገር የመጡ ዳያስፖራዎችም በሽብር ቡድኑ ወረራ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ በሚገኙ  የአጣዬ፣ ሸዋሮቤት፣ ካራ ቆሬ እና ደብረ ሲና ከተሞች ላይ በአካል በመገኘት የደረሰውን ጉዳት ተመልክተዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች ዜጎች ንብረታቸው ከመውደሙ ባሻገር ከፍተኛ የሆነ የሞራል ጉዳት እንዳጋጠማቸው መታዘባቸውንም ተናግረዋል።

በርካታ አረጋዊያን፣ ሴቶች እና ህጻናት የወገኖቻቸውን ድጋፍ አጥብቀው የሚሹበት ሁኔታ ላይ እንዳሉም ተመልክተናል ብለዋል።

እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች መልሶ የማቋቋም እና የሞራል እገዛ ማድረግ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑንም  ጠቁመዋል።

በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩላችንን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን  ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ የተጎዱ ዜጎችን በሁለንተናዊ መልኩ ለማገዝ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ለመተግበርም እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ዳያስፖራው በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቹን በመደገፍ ረገድ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም