የሕብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን ለማስገንዘብ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል

155

ጥር 20 ቀን 2014(ኢዜአ) የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን እንዲገነዘብ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

አዲስ አበባ ጉባኤውን ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃ እንግዶቿን ለመቀበል እየተጠባበቀች መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል።

በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ የሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ጥር 28 እና 29 ቀን 2014 ዓ.ም ሲካሄድ  የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባ ደግሞ ቀደም ብሎ ጥር 25 እና 26 ይካሄዳል።

ለዚህ ታላቅ ጉባኤ አዲስ አበባ ዝግጅቷን አጠናቃ የእንግዶቿን መምጣት በመጠባበቅ ላይ መሆኗን የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዮናስ ዘውዴ ገልጸዋል።

የመሪዎቹ ጉባኤ በውቧ አዲስ አበባ በአስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ እንዲካሄድ ለማስቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ሁለንተናዊ ዝግጅት መደረጉን አክለዋል።

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ደግሞ ከተማዋን በማስዋብ ላይ መሆናቸውን ገልጸው አዲስ አበባ አምራና ተውባ እንግዶቿን ለመቀበል ተዘጋጅታለች ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ጉባኤው የተሳካ እንዲሁን ግብረ ሃይል አቋቁሞ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

የጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄድ ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን የዓለም ማህበረሰብ በአግባቡ የሚረዳበት አጋጣሚ በመሆኑ እድሉን ለመጠቀም ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠይቋል።

በጉባኤው የኮቪድ-19 መከላከል ፕሮቶኮል በአግባቡ መተግበር ስላለበት ህዝቡ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ እንዲንቀሳቀስ አቶ ዮናስ አሳስበዋል።

በከተማ አስተዳደሩ በኩል ወረርሽኙን በመከላከል ሂደት ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች፣ የመዝናኛ ስፍራዎች የኮቪድ ፕሮቶኮልን መጠበቅ አለባቸው፤ ለዚህም ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።

የዘንድሮው የመሪዎች ጉባኤ “የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ያፋጥናል” በሚል መሪ ቃል ይካሄዳል።