ሰዎች ለሰዎች በኢትዮጵያ ለሰብአዊና ለሌሎች አገልግሎቶች ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል

86

ጥር 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ለሰብአዊና ለተቀናጀ የገጠር ልማት አገልግሎት ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ተገለጸ።

ላለፉት 40 ዓመታት በኢትዮጵያ በተቀናጀ የገጠር ልማት አገልግሎትና በሰብአዊ ድጋፍ ስራዎች ላይ ተሳትፎ የሚያደርገው ሰዎች ለሰዎች ድርጅት በውሃ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃና በሰው ሃብት ልማት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ እንዳደረገ የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሙሉነህ ቶሎሳ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሀላፊው እንዳሉት፤ ድርጅቱ በታዋቂው የፊልም ተዋናይ ካርልሄንዝ በም ከተመሰረተበት ከ1970ቹ አንስቶ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሚገኙ ዜጎች ቀጥተኛ ድጋፍና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን አከናውኗል።

ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግንባታና ቋሚ ድጋፍ፣ የውሃ አቅርቦት፣ የመንገድ ጠረጋ፣ የጤና ተቋማትና ሆስፒታሎች ግንባታ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ድርጅቱ ባለፉት 40 ዓመታት ያከናወናቸው ተግባራት ናቸው ብለዋል።

በነዚህ ተግባራትም “ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል፣ 6 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ በቀጥታ ተጠቃሚ ሆነዋል” ነው ያሉት ሃላፊው።

በአሁኑ ወቅት 13 ፕሮጀክቶች በስራ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፤ የአካባቢ ጥበቃ፣ የመስኖ ልማት፣ ውሃ አቅርቦት እና የወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ድርጅቱ ትኩረት አድርጎ የሚሰራባቸው ዘርፎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የድጋፍና የቋሚ ተጠቃሚነት ፕሮጀክቶቹ ከመንግስት ጋር በቅንጅት እንደሚከናወኑ ያወሱት አቶ ሙሉነህ፤ መንግስት ቅድሚያ ያስፈልጋቸዋል ብሎ በለያቸው አካባቢዎችና የድጋፍ አይነቶች መነሻነት ድርጅቱ እንደሚንቀሳቀስ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም