ምክር ቤቱ 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አጸደቀ

82

ጥር 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለትን የፌዴራል መንግስት 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሦስተኛ ልዩ ስብሰባውን አካሂዷል።

በዚህም የቀረበለትን የፌዴራል መንግስት 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል።

አጠቃላይ ጭማሪ በጀቱ 122 ቢሊዮን ብር ሲሆን ለመደበኛ ወጪ 106 ቢሊዮን፣ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ለሚደረገው ፕሮጀክት ማስጀመሪያ 5 ቢሊዮን ብር፣ ለግድብና መስኖ አውታር ጥገና ፕሮጀክት 2 ቢሊዮን ብርና ቀሪው ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውል ነው።

በበጀት ጭማሪው አስፈላጊነት ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን ጭማሬው የዋጋ ግሽበቱን እንዳያባብስ ሲሉም ስጋታቸውን ጠቅሰዋል።

የበጀት ጭማሪውን ድልድል በተመለከተ በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች እርዳታና የወደሙ መሰረተ ልማትን መልሶ ለመገንባት የተያዘው 5 ቢሊዮን ብር ከጉዳቱ አንጻር በቂ አለመሆኑንም አንስተዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ፤ የምክር ቤቱ አባላት ላነሱት ጥያቄ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የበጀት ጭማሪው የዋጋ ግሽበትን እንዳያባብስ መንግስት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረጉን ተናግረዋል።

ከብሔራዊ ባንክ አዲስ ገንዘብ ታትሞ ወደ ገበያ የሚገባ ሳይሆን በአሁኑ ወቅት ገበያ ላይ ያለን ገንዘብ ለመጠቀም ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።

በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ከበርካታ አጋር አካላት ገንዘብ እየተሰባሰበ መሆኑን ጠቁመው  5 ቢሊዮኑ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ መሆኑን አስረድተዋል።

በጀቱ ለአገር ደህንነት ማስጠበቂያ፣ ለሰብዓዊ እርዳታ፣ በጦርነትና ግጭቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ማቋቋሚያ እንዲሁም ለሌሎች አስፈላጊ የመንግስት ሥራዎች ማስፈጸሚያ መዋሉ አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን አባላቱ አስተያየት ሰጥተዋል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የፌደራል መንግስት ተጨማሪ በጀትና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የቀረበለትን የፌደራል መንግስት 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት በዘጠኝ ተቃውሞና  በሰባት ጽምፀ ተአቅቦ  በአብላጫ ድምፅ  ጸድቋል።

አዋጁ የመንግስት ተጨማሪ በጀትና የወጪ አሸፋፈን ለማስተካከል ከአገር ውስጥ ብድር እንዲሸፍን ይፈቅዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም