የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአማራ ክልል በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችንና የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ዝግጅት ጀምሯል

79

ጎንደር፣ ጥር 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችንና የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋም በመንግስት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ዝግጅት መጀመሩን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አስታወቀ።

በማህበሩ የሰሜን ጎንደር ቅርንጫፍ የቦርድ አመራሮች ጠቅላላ ጉባኤ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።

በማህበሩ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ ሻምበል ዋለ በጉባኤው ላይ እንደተናገሩት፤ ማህበሩ በክልሉ በጦርነቱ  የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት በማቋቋምና የወደሙ ተቋማትን መልሶ በማቋቋም ሥራ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ኮሚቴ አዋቅሮ የቅድመ ጥናት ሥራዎችን ጀምሯል፡፡

የቅድመ ጥናት ስራዎቹ በተለይ በአማራ ክልል በሰሜንና ደቡብ ወሎ እንዲሁም በዋግ ህምራና በሰሜን ጎንደር ዞኖች ጦርነቱ በደረሰ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ማህበሩ በትምህርት፣ ጤናና የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት በጥናት በመለየት ከየካቲት ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ በመልሶ ግንባታ ስራ ይሳተፋል።

በጦርነቱ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በአጭር ጊዜ ለማቋቋም የእርሻ በሬዎቻቸው የሞቱባቸውና የተዘረፈባቸውን የመደገፍ ስራ እንደሚከናወን አመለክተዋል።

እንደ አቶ ሻምበል ገለጻ፣ ማህበሩ መኖሪያ ቤታቸው ለተቃጠለባቸው ወገኖች አዳዲስ የመኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ወደ ቀደመ ህይወታቸው እንዲመለሱ የሰብአዊ ድጋፍ ያደርጋል።

ማህበሩ በመልሶ ማቋቋም መርሃ ግብሩ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የሚሆን ድጋፍ ከ7 ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ቃል እንደተገባለት አስረድተዋል፡፡

ማህበሩ ባለፉት ስድስት ወራት በጦርነቱ ሰለባ ለሆኑና ከ300 ሺህ ለሚበልጡ ተፈናቃይ ወገኖች ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምግብና ሌሎች ሰብአዊ ድጋፎችን አድርጓል።

በጦርነቱ ተፈናቅለው በደባርቅ ጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ከ60 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ መደረጉን የተናገሩት ደግሞ በማህበሩ የሰሜን ጎንደር ቅርንጫፍ ሃላፊ አቶ አታለል ታረቀኝ ናቸው።

ቅርንጫፉ በጠቅላላ ጉባኤው የሥራ ዘመናቸውን ባጠናቀቁ የቦርድ አመራሮች ምትክ የቦርድ አባላት ምርጫ እንደሚያካሂድ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም