የአሶሳ ነዋሪዎች የአስፓልት መንገድ ግንባታና ደረጃ ማሻሻል ፕሮጀክት ፈጥኖ እንዲጀመር ጠየቁ

78

አሶሳ ጥር 19/2014 (ኢዜአ ) በአሶሳ ከተማ ለአዲስ አስፓልት መንገድና የነባሩን መንገድ ደረጃ ለማሳደግ የተያዘው የግንባታ ፕሮጀክት ፈጥኖ ወደስራ እንዲገባ ነዋሪዎች ጠየቁ።

በአሶሳ ከተማ በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር አዲስ የአስፓልት መንገድ ለመገንባትና፣ የነባሩን ደረጃ ለማሳደግና ለመጠገን የመሰረተ ድንጋይ ተቀምጧል።

የመንገዱን ግንባታ አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ዘውዱ መኮንን ለግንባታው የመሰረተ ድንጋይ ሲቀመጥ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በከተማዋ በመንገድ ብልሽት ምክንያት ታክሲዎች ወደአካባቢያቸው እንደማይገቡ ጠቅሰው፣ በመንገድ ብልሽቱ በተለይ አቅመ ደካሞችና ነፍሰ-ጡሮች ወደ ህክምና ተቋም ሲሄዱ እየተንገላቱ መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩ እንዲፈታ የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠለት የመንገድ ፕሮጀክት ፈጥኖ ተጀምሮ ለአገልግሎት እንዲበቃ ጠይቀዋል፡፡

አቶ አማኑ ሁሴን እና አቶ ጀማል ኑሪየ የተባሉ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው ሃላፊነት የጎደላቸው አንዳንድ ነዋሪዎች በፍሳሽ ማስወገጃ ትቦዎች የሚጥሉት ቆሻሻ የመንገዱን ብልሽት እያባባሰው መሆኑን ተናግረዋል።

የከተማውን መሰረተ ልማት ለማሻሻል በሚደረጉ የተለያዩ የውይይት መድረኮች ላይ መሳተፋቸውን አስታውስው፣ አስተዳደሩ የከተማው ነዋሪ ለመንገዱ ግንባታ ተግባራዊነት ድጋፍ የሚያደርግበትን ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቀዋል።

የመንገዱ መበላሸት ለተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው፣ የተሸከርካሪ አካል ክፍሎች ለረዥም ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጡ እየተሰበሩና ለወጪ እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ለማ አልጋ የተባሉ ሌላው የአሶሳ ከተማ ነዋሪ የከተማው አስፓልት መንገድ ከከተማዋ መስፋፋትና የህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር እንደማይመጣጠን ተናግረዋል።

ልማት ያለ ህዝብ ተሳትፎ ውጤታማ እንደማይሆን ተናግረው፣ ለእዚህም ከተማ አስተዳደሩ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

ከከተማዋ መስፋፋት ጋር በተያያዘ በየአካባቢው መንገድ ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት በአስተዳደሩ በኩል ነዋሪዎችን ያሳተፉ ሥራዎች ሊከናወኑ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ኢዜአ ከአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱልሙኒየም አብዱልዋሂድ በጉዳዩ ላይ መረጃ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ከንቲባው ባለመገኘታቸው ምክንያት ሊሳካ አልቻለም።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አሸሪፍ ሃጂአኑር ከስድስት ወራት በፊት ለከተማው አዲስ የአስፓልት መንገድ፣ ደረጃ ማሳደግና ጥገና ሥራ የመሰረተ ድንጋይ መቀመጡን አስታውሰዋል።

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በነበረው አለመረጋጋት የመንገዱ ግንባታ በተወሰነ ደረጃ ቢስተጓጎልም በአሁኑ ወቅት ሥራው እንዲጀመርና በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የሥራ ተቋራጩ የቅድመ ግንባታ ዝግጅት ሥራዎች እያካሄደ መሆኑን ጠቁመው፣ በቅርቡም የአዲስ አስፓልት መንገድ ስራው እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡

አቶ አሸሪፍ እንዳሉት በቀጣይ ሦስት ዓመታት ስራው ሙሉ ለሙሉ እንዲጠናቀቅ በትኩረት ይሰራል።

አቶ አሸሪፍ አክለው የክልሉ መንግስት የከተማው አስፓልት መንገድ ግንባታ በተቀመጠለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የመንገዱን ግንባታ የሚያከናውነው ክሮስላንድ ኮንስትራክሽን የአሶሳ መንገድ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲስ አጋፋሪ፣ በፕሮጀክቱ የሚካሄደው አጠቃላይ መንገድ 20 ኪሎ ሜትር እንደሚጠጋ ገልጸዋል።

እንደሳቸው ገለጻ አራት ኪሎ ሜትር ያህል አዲስ አስፓልት፣ ከዘጠኝ ኪሎ ሜትር በላይ ደረጃ ማሻሻል እንዲሁም የሰባት ኪሎ ሜትር የጥገና ስራ ይከናወናል።

ባለፉት ሁለት ወራት የቢሮ ግንባታ፣ የሠራተኛ ቅጥር፣ የመሳሪያዎች አቅርቦት፣ የቅየሳና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በቅርቡ የቅድመ ዝግጅት ሥራው እንደሚጠናቀቅና ከሁለት ወራት በኋላ ዋናው የአስፓልት መንገድ ሥራ እንደሚጀመር ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል፡፡

"በክረምት ወቅት ሊከሰት የሚችለውን የሥራ መስተጓጎል ለማካካስና ግንባታውን በወቅቱ አጠናቆ ለማስረከብ ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን" ብለዋል።

100 ሺህ የሚሆን ህዝብ እንደሚኖርበት የሚነገርላት የአሶሳ ከተማ ከ15 ዓመት ወዲህ የተገነቡ ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ አስፓልት መንገድ እንዳላት መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም