በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የኮቪድ-19ን ፕሮቶኮል በአግባቡ በመተግበር ለመከላከል አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል

61

ጥር 19 ቀን 2014 (ኢዜአ)በዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የኮቪድ-19ን ፕሮቶኮል በአግባቡ በመተግበር ለመከላከል አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

በጉባኤው የተሳታፊዎችን ጤንነት ለመጠበቅ በየእለቱ ፈጣን የኮቮድ-19 ፈጣን ምርመራ ይደረጋል ተብሏል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላለፉት ዓመታት የፊት ለፊት ስብሰባ ሳይካሄድ እንደቆየ ይታወቃል።

35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ በመወሰኑ ጉባኤው በተሳካ መልኩ እንዲካሄድ ኢትዮጵያ ዝግጁ ሆናለች።

በጉባኤው ላይ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚኖረውን ተጽእኖ ለመከላከል ፕሮቶኮሉን በአግባቡ በመተግበር ስብሰባው በጥሩ ሁኔታ እንዲካሄድ በኢትዮጵያ በኩል አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገልጸዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች ሁሉ የምርመራ ውጤት እና የክትባት ሰርተፊኬት ይዘው መምጣት ግድ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንግዶች ኤርፖርት ሲገቡ እና በሚያርፉባቸው ሆቴሎች እንዲሁም ስብሰባው በሚካሄድባቸው ቀናቶች ሁሉ አስፈላጊውን የኮቪድ መከላከል ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚደረግ መሆኑን ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።

እንግዶችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ ሆቴሎች የኮቪድ ፕሮቶኮልን በመጠበቅ ማስተናገድ እንዲችሉ ከቱሪዝም ሚኒስቴር፣ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከሌሎችም አካላት ጋር በመወያየት መመሪያ ወጥቷል፤እንዲተገበርም ይደረጋል ብለዋል።

በከተማዋ እንቅስቃሴ ላይ ማህበረሰቡ በትራንስፖርት እና በሌሎችም የህዝብ መገልገያ ስፍራዎች ላይ አስፈላጊውን የመከላከል ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።

በጉባኤው የተሳታፊዎችን ጤንነት ለመጠበቅ ከአፍሪካ በሽታ መቆጣጠር ማዕከል ጋር በመተባበር በየእለቱ ፈጣን የኮቮድ-19 ምርመራ ይደረጋል ብለዋል።

የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ የሚመክር ሲሆን በተለይም በምግብ ዋስትና ፕሮግራም፣በአህጉራዊ የሰላምና የጸጥታ ጉዳዮች እና በአጀንዳ 2063 አፈጻጸም ባሉ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል።

የህብረቱ የሰላምና የጸጥታ ምክር ቤት አባላትና ሌሎችም ምርጫዎች የሚካሄዱበት መሆኑ ታውቋል።

የዘንድሮው የመሪዎች ጉባኤ “የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፤ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ያፋጥናል” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚካሄደው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም