ተቋማቱ በግዥና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በጋራ ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

186

ጥር 19/2014/ኢዜአ/ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን እና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በግዥና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በጋራ ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ እና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለ ተፈራርመዋል።

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ በዚህን ወቅት እንዳሉት፤ 65 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ በጀት ለተለያዩ አገልግሎቶች ለሚውሉ ግብአቶች ግዥ የሚወጣ ነው፡፡

ከ2014 ዓ.ም የመንግስት በጀት ውስጥ 351 ቢሊዮኑ ለተለያዩ ግዥዎች እንደሚውልም ነው የተናገሩት።

በመሆኑም የአገሪቷ ከፍተኛ ሃብት የሚፈስበት የግዥ ስርዓት ወጪ ቆጣቢና ከሌብነት በፀዳ መልኩ መፈጸም አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ስምምነቱ የንብረት ግዥን ከለላ በማድረግ የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን ለመቆጣጠር ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በተጨማሪ ከጨረታ ውጭ ህጋዊ መስመሩን ሳይከተል ግዥ የሚፈጽሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡

ባለስልጣኑ በቀጣይ ከስነ ምግባርና የጸረ-ሙስና ተቋምና ከፌደራል የወንጀል ምርመራ ፖሊስ ጋር መሰል ስምምነቶችን እንደሚፈራረምም አቶ ሃጂ ኢብሳ ገልጸዋል፡፡

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለ በበኩላቸው በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ሃብትን ፣ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትና የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን በገንዘብ መደገፍ በዋናነት ተቋሙ የሚከላከላቸውና የሚቆጣጠራቸው ተግባራት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ ብቻውን በመስራት ውጤታማ መሆን እንደማይችል ጠቅሰው፤ በዚህም ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ማድረግ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረገው ስምምነት ዘመናዊ የቁጥጥር ስርዓትን ከመገንባት አኳያ የላቀ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአገሪቱ የሚፈጸሙ በርካታ ግዥዎችን በማስታከክ የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችንና የተንዛዛ አሰራርን ለማስቀረት እንደሚያግዝም እንዲሁ፡፡

በዘርፉ ዓለም የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም