በአሸባሪው ህወሃት ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የህግ ከለላ ለመስጠት ብሔራዊ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል

64

አዲስ አበባ ጥር 19/2014(ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሃት ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የህግ ከለላ ለመስጠት ብሔራዊ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ።

አሸባሪው ህወሃት በወረራ በቆየባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ሁሉ ዘረፋና ውድመት ከማድረሱ በተጨማሪ ታዳጊ ህፃናትን ጨምሮ በሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት ፈፅሟል።

የጦርነት አስከፊ ገጽታ ከሚበረታባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል በተለይ ሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጮች ይሆናሉ።

በመሆኑም አሸባሪው ህወሃት በወረራ በቆየባቸው የአማራና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በሴቶች ላይ ጭካኔ የታየባቸውን ወንጀሎች መፈፀሙን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገልጸዋል።

በሽብር ቡድኑ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞችና ህጻናትም ለከፋ ጉዳትና የስነ-አእምሮ ችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ህፃናትና ሴቶችን በደል ከማከም በተጨማሪ የህግ ከለላና ካሳ በማስፈለጉ ጉዳዩን የሚከታተል ግብረ ሃይል መቋቋሙን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ግብረ ሃይሉ በፍትህ ሚኒስቴር የሚመራ ሲሆን የኢትዮጵያና ዓለም ዓቀፉ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በጋራ ባወጡት ሪፖርት ላይ በመመስረት ምርመራ እንደሚያካሂድም ተናግረዋል።

በዋናነት ግብረ ሃይሉ የችግሩን ስፋት ከመመርመር ባሻገር የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሴቶች የህግ ከለላ እንዲያገኙ ይሰራል ብለዋል።

አጥፊዎችን በተገኙበት ሁኔታና ቦታ ተጠያቂ የማድረግና ተጎጂዎችም ከሚሰጣቸው የህክምና እርዳታ ባሻገር የካሳ ክፍያ እንዲያገኙ ለማድረግ ይሰራል ነው ያሉት።

አሸባሪው ህወሃት ለ27 ዓመታት ህዝቡን በልዩነት ለማጠር ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው አሁንም አገር ለማፍረስና በዜጎች ላይ ግፍ በማድረስ በክህደቱ ቀጥሎበታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ቀደም ሲል ትኩረት ተነፍጓቸው የነበሩ የእርቅና አብሮነት ባህላዊ እሴቶችን አሁን ላይ ከዘመናዊው አሰራሮች ጋር በማጣመር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዘላቂ አገራዊ ሰላም ሴቶች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የላቀ በመሆኑ ተሳትፎና እገዛቸውን በማጠናከር ለብሄራዊ መግባባት አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም