“የተጎዳ መሬትን አልምቶ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ በራሱ የህልውና ዘመቻ ነው”

111

አሶሳ ፣ ጥር 19/2014 (ኢዜአ) የተጎዳ መሬትን አልምቶ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ በራሱ የህልውና ዘመቻ ነው” ይላሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አርሶ አደሮች።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በበጋ ወራት አካፋ እና ዶማ ይዘው በየጉድባው የሚተሙ ትጉህ አርሶ አደሮችን መመልከት የተለመደ ዓመታዊ ትዕይንት ነው፡፡
ቁጭት እና እልህ ፊታቸው ላይ የሚነበበው አርሶ አደሮች በተለይ ካለፉት ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች የተራቆቱና የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ እንዲያገግሙ ከማድረግ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዲሰጡ የማድረግ ስራ እያደገ መጥቷል፡፡
በክልሉ በየአካባቢው የሚከናወን የበጋ ተፋሰስ ልማት ግንባታው በመገባደድ ላይ ላለውና ፍሬው በጉጉት ለሚጠበቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከደለል ለመከላከል ጭምር የገዘፈ ፋይዳ ያለው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ይህንን ትልቅ ተሻጋሪ ራዕይ ያነገቡት የክልሉ አርሶ አደሮች ከሰሞኑ በክልሉ አሶሳ ወረዳ አፋ ተፋሰስ ላይ ተሰባስበው የተለመደውን ዓመታዊ ዘመቻ በከፍተኛ ተነሳሽነት በይፋ ጀምረዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ የዘመቻቸው ትኩረት ያደረጉት መሰል የተጎዱ ቦታዎችን ነው፡፡
በዚሁ ተፋሰስ ከተራራማ የእርሻ መሬት መሀል ተነስቶ እስከ ጎርፍ መውረጃ ድረስ ከአምስት ሜትር በላይ ጥልቀት ያለው ትልቅ ሸለቆ ይታያል፡፡ አርሶ አደር አደም መንሱር በተፋሰስ ልማቱ ዘመቻው ከተሳተፉት አንዱ የሆኑት የአሶሳ ወረዳ የአፋ መገሌ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው “ከ40 ዓመት በፊት እኔ ልጅ እያለሁ ይህ አካባቢ በሙሉ ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነ ነበር” ይላሉ፡፡ አርሶ አደሩ ይህ የምትመለከተው ቦታ አፈሩ በዝናብና በነፋስ ለረጅም ዓመታት እየታጠበና እየተጠረገ በመሄዱ የተፈጠረ ሸለቆ ነው ሲሉ የተጎዳውን የእርሻ ማሳ ያመላክታሉ፡፡
አርሶ አደር አደም እንዳሉት ለአካባቢው መራቆት ተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚስተዋለው ደካማ አጠቃቀም በዋና ምክንያትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በመሆኑም የወደመውን የተፈጥሮ ሀብት መልሶ የመተካት ሀላፊነት “የእኛ እንጂ የሌላ የማንም አይደለም፡፡” ነው ያሉት፤ የችግሩ መንስኤም የመፍትሔ አካልም ራሱ ኅብረተሰቡ እንደሆነ በመጠቆም።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፋሰስ ስራዎች የተቦረቦረ መሬት አገግሟል፤ የነጠፉ ምንጮች እንደገና መታየት ጀምረዋል፤ እፅዋቱም እየለመለሙ ነው፡፡ በዓባይ ተፋሰስ ዋነኛ ገባር በሆነው ዳቡስ ወንዝ አቅራቢያ እንደሚኖሩ የሚናገሩት አርሶ አደሩ የተፋሰስ ስራችን በጎርፍ በታጠበ አፈር ከደፈረሰ ይልቅ ንጹህ ውሃ ወደ ዓባይ ወንዝ እንዲፈስ ከመፈለግ ነው፡፡ "ይህም የህዳሴ ግድባችንን ከደለል እንደሚታደግ ከተረዳን ዓመታትን አስቆጥረናል" ይላሉ፡፡ የጀመርነው የተፋሰስ ልማት ስራ ለትውልድ የሚተላለፍ ነው ያሉት አርሶ አደር አደም ጥቅሙን በሚገባ ስለተረዳን ስራውን ሳናቋርጥ ከመቀጠል የሚያስቆመን የለም ሲሉ በአፅንዖት ያረጋግጣሉ፡፡
በየዓመቱ በሁለት ተከታታይ ወራት ውስጥ በሳምንት ሁለት ቀናትን ያለማንም ቅስቀሳ ለበጋ ተፋሰስ ልማት ስራ እናውላለን የሚሉት ደግሞ የመገሌ 31 ቀበሌ አርሶ አደር ያሲን ኢማም ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ እንደሚሉት የተጎዳን መሬት በአግባቡ በማልማትና በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍ በራሱ የህልውና ዘመቻ ነው፡፡ “ወንድሞቻችን በአማራ እና አፋር ክልሎች ሽብርተኛውን ህወሓት በማስወገድ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው፡፡ እኛም እያከናወንን የምንገኘው የተፋሰስ ስራ፥ ለመጪው ትውልድ ምቹና ለምለም ሀገርን ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ የህልውና ዘመቻ ነው ” ይላሉ፡፡
በበጋ ተፋሰስ ስራ በፈቃዳቸው እየተሳተፉ እንደሚገኙ የሚናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ወይዘሮ ጠይባ ኢስሃቅ ናቸው፡፡ “በእጄ ያለውን የእርሻ መሬት አልምቼ ነው ለሶስት ልጆቼ የማስተላልፈው፡፡ ከምንም በላይ ዓላማዬ ያደረኩት ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራውን ያሳረፈበት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአካባቢ መራቆት ምክንያት ሊያጋጥመው የሚችለውን በደለል የመሞላት ስጋት መከላከል ነው ሲሉ ነው ውጥን ራዕያቸውን የገለጹት፡፡
የክልሉ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ከሊፋ በክልሉ የበጋ ተፋሰስ ልማት ስራ የተጀመረው በ2011 ዓ.ም. መሆኑን ያስታውሳሉ፡፡ በእነኚህ ዓመታት 309 ሺህ 827 ሄክታር የተራቆተ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ ተከናውኗል፡፡ በተፋሰስ ልማት ስራው ላይም አርሶ አደሮችን ጨምሮ አብዛኛው የክልሉ ህዝብ መሳተፉን ይገልጻሉ ፡፡
በዚህ ዓመት በተፋሰስ ልማት ስራው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ያህል አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ። በዚህም ከ44 ሺህ 300 በላይ ሄክታር የተጎዳ መሬት በበጋ የተፋሰስ ልማት ዘመቻ ስራ ይሸፈናል፡፡ ዕቅዱ እንደሚሳካም እርግጠኛ ናቸው፡፡ እርግጠኛ የሆኑት ደግሞ አርሶ አደሮች በየዓመቱ በዘመቻ የሚያካሂዱት የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ስራ መጨመሩንና ከጥቅም ውጪ የሆኑ ስፍራዎች መልሰው በማገገም ጥቅም ላይ በመዋላቸው ነው፡፡
በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በለሙ ተፋሰሶች ወጣቶችን ጨምሮ ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንስሳትን የማደለብ፣ ንብ በማነብ እና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ስራዎችን መፍጠሩን አቶ ባበክር በአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ አብዛኛው የተፋሰስ ልማት የተካሄደው በወል መሬት ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ዓመት ተሞክሮውን በአርሶ አደሮች የግል ማሳ ላይ ማስፋት ትኩረት እንደተሰጠው አስረድተዋል፡፡ በየደረጃው የሚገኘው አመራርና በየቀበሌው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች አቅማቸውን አሟጠው አርሶ አደሩን እንዲደገፉ ጠንካራ የክትትል አቅጣጫ መቀመጡንም ኃላፊው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ክልሉን ከሽፍቶች በማጽዳት የአካባቢውን ሠላምና ፀጥታ ለመጠበቅ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የተፈጥሮ ሀብት እንክበካቤ ስራው ከዚህ በተጓዳኝ የሚደረግ ትግል ነውም ይላሉ፡፡
“ግጭት የተወሰኑ ወገኖቻችንን ነው የሚጎዳው፡፡ ረሃብ ግን ሁላችንንም የማጥፋት አቅም አለው፡፡ ረሃብን መከላከያው ዋነኛው መንገድ ደግሞ የተፈጥሮ ሀብታችንን በዘላቂነት በመጠበቅ ግብርናውን ማዘመን ነው፡፡ ሀገርን ለማፍረስ በተነሳው በሽብርተኛው ህወሓት ላይ በአንድነት ያገኘነውን ድል ተፈጥሮ ሃብታችንን በማልማት ላይ መድገም አለብን” ሲሉ አርሶ አደሮቹ የጀመሩትን ጥረት እንዲያጠናክሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአግባቡ ከለማ ከራሱ አልፎ ኢትዮጵያን መመገብ የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብት እንዳለው የሚናገሩት ደግሞ የተፋሰስ ልማት ዘመቻውን ያስጀመሩት የግብርና ሚኒስቴር ተወካይ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤሊያስ ናቸው፡፡ በመልዕክታቸው እንዳሉት “ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች በምግብ ሰብል ራሳችንን እንዳንችል አድርገውናል። ይህም በውጭ እርዳታ ጫና ስር እንድንወድቅ አድርጎናል ይላሉ፡፡
ተላላኪ እና ተንበርካኪ መንግሥት የሚፈልጉት አንዳንድ ኃያላን ሀገሮች እርዳታ በመስጠት እጃችንን ሊጠመዝዙ መሻታቸው ለዚሁ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ኢያሱ፡፡ ይህ ሁላችንንም በእጅጉ ሊቆጨንና ሊያንገበግበን ይገባል” ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ሉዓላዊነትን ለማስከበር አንዱ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ መሠረቱ የሆነውን የተፈጥሮ ሀብታችንን በአግባቡ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ግድቦቻችንን ከደለል መጠበቅ ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም