ምክር ቤቱ አዳዲሶቹን ክልሎች ለመደገፍ እየተንቀሳቀሰ ነው

144

ሀዋሳ፣ ጥር 18/2014 (ኢዜአ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአዳዲሶቹን ክልሎች ክፍተቶች ለይቶ ለመደገፍ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ዘሃራ ሁመድ አስታወቁ።


የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔዋ ከምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን ከሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር፣ ከክልሉ ካቢኔና ከምክር ቤት አባላት ጋር ተወያይተዋል።


ምክትል አፈ ጉባዔዋ ፌዴሬሽኑ የክልሉ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ተከብሮ ክልላዊ መንግሥት ከተመሰረተ በኋላ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ መገምገሙን ተናግረዋል።


በተለይ ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ ያስመዘገባቸውን ጥንካሬዎችን በመለየትና ክፍተቶች በሚስተካከሉበት መንገድ የጋራ ስምምነት ላይ መደረሱን ወይዘሮ ዘሃራ አመልክተዋል።


ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች ከሚሰጠው ድጎማ የተወሰነው ለልማት ሥራዎች ለማዋል የራሱን አቅጣጫ ለማስቀመጥ ጥናት እያስደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


"ጥናቱ ሲጠናቀቅ አዳዲስ ክልሎች ያሉባቸውን ክፍተቶች ለመሙላት ቅድሚያ ተሰጥቶ ይሰራል" ብለዋል።


ክልሉ ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት ያላቸው ሴክተሮች ላይ በመሥራት የሕዝብን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ እንዲሰራ ወይዘሮ ዘሃራ አስገንዝበዋል።


ፌዴሬሽኑ የሕዝቦችን እኩልነት ለማረጋገጥና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት ለማጠናከር ጥረቱን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።


የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ በክልሉ በልማት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሰላምና ጸጥታ ሥራዎች ዙሪያ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ልዑካን ጋር በመወያየት ቀጣይ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ተናግረዋል።


የክልሉ ሕዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ ሕዝቡ ሰላም ያገኘበት፣ወደ ልማቱ መመለሱን በመጥቀስ፥ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ያለውን አንድነት ማጠናከሩን ወይዘሮ ፋንታዬ አመልክተዋል።


የሲዳማ ክልል የቀጣዩ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አዘጋጅ እንደመሆኑ በዓሉ ኅብረ ብሄራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እንዲከበር መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ምክክር መደረጉም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም