በባሌ ዞን ከ13 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞች ለተከላ ዝግጁ ነው

113

ጎባ ፣ ጥር 19/2014(ኢዜአ) በባሌ ዞን የቡና ልማትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከ13 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የቡናና ቅመማ ቅመም ልማትና ጥራት ቡድን መሪ አቶ ወንደሰን ነጋ ለኢዜአ እንደገለጹት እየተዘጋጁ ያሉት ችግኞች ከግብርና ምርምር ማዕከላት የተገኙና በሽታን ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡ የተሻሻሉ ዝርያዎች ናቸው።

በክረምት ወቅት የሚተከሉት የቡና ችግኞች ከ1 ሺህ 500 በሚበልጡ የመንግስትና የግለሰብ የችግኝ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸው፣ በዞኑ የቡና ልማትን ለማስፋፋትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዘንድሮ አዲስ የሚተከሉት የቡና ዝርያዎች ከነባሩ ዝርያ በሄክታር እየተገኘ ያለውን አምስት ኩንታል ምርት በእጥፍ ወደ አስር ኩንታል የማሳደግ አቅም ያላቸው እንደሆኑም አስረድተዋል።

በክረምቱ ወራት የሚተከሉት እነዚሁ የቡና ችግኞች ከምርምር ማዕከላት የተለቀቁ “ሞካ”ና “ዴሱ” የሚባሉትን ጨምሮ 15ቱ የተሻሻሉ ዝሪያዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።

የቡድን መሪው እንዳሉት የቡና ችግኞቹ ከመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ በ2 ሺህ 690 ሄክታር አዲስ መሬትን በቡና ተክል ለመሸፈን ለተያዘው ውጥን ስኬት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡

በቡና ችግኝ ዝግጅትና እንክብካቤ ሂደቱ እየተሳተፉ ከሚገኙ ከ24 ሺህ በላይ አርሶና አርብቶ አደሮች መካከል 1 ሺህ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በዞኑ በአሁኑ ወቅት በቡና ተክል ከተሸፈነው 54 ሺህ ሄክታር ማሳ ውስጥ 65 በመቶ ምርት የሚሰጥ ነው፡፡

በክልሉ ዘንድሮ የቡና ልማትን ለማስፋፋት ከ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የቡና ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ መሐመድ ሳኒ አሚን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ዘንድሮ የቡና ልማትን ለማስፋፋት ከ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የቡና ልማት ተናግረዋል፡፡

አስተባባሪው እንዳሉት እስከ አሁን በተደረገው ጥረት በክልሉ ቡና አብቃይ በሆኑ 18 ዞኖች ውስጥ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን የቡና ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል፡፡

ለተከላ የተዘጋጁ ችግኞች ከግብርና ምርምር ማዕከላት የተገኙ የተሻሻሉ ምርት የሚሰጡ ከመሆናቸው በተጓዳኝ ከ160 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ አዲስ መሬት በቡና ተክል ለመሸፈን እንደሚያስችሉም አስረድተዋል፡፡

በዞኑ ደሎ መና ወረዳ በቡና ልማቱ ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ያሲን ዳውድ በሰጡት አስተያየት በቡና ልማት ስራ የቆየ ልምድ ቢኖራቸውም ከምርምር ማዕከላት የተለቀቁ ዝርያዎችን ስለማያገኙ የልፋታቸውን ያክል ተጠቃሚ እንዳልነበሩ አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን ከመንግስት ያገኙትን የተሻሻሉ የቡና ዝርያ ችግኞችን ያረጁ የቡና ተክሎችን በመንቀል ለመትከል ችግኝ እያዘጋጁ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

የቡና ችግኝ ከማዘጋጀት ጀምሮ ባለሙያዎች በቅርበት ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላው የልማቱ ተሳታፊ አቶ በከር ከማል ናቸው፡፡

በተለይ አሁን የተሻሻሉ ምርት እንደሚሰጡ የተነገረላቸውን የቡና ዝርያዎች የግብርና ባለሙዎች በሰጧቸው ሙያዊ ምክር በመታገዝ የእንክብካቤ ስራ እያካሄዱ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ቡና አብቃይ በሆኑ 18 ዞኖች ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በቡና ተክል የተሸፈነ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታሩ ምርት የሚሰጥ መሆኑን ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም