አሸባሪው ህወሀት በህዝብና በሀገር ላይ ያደረሰውን ግፍ ለዓለም ማህበረሰብ እናሳውቃለን --ዳያስፖራዎች

117

ደሴ፣  ጥር 18/2014 (ኢዜአ) --'በአሸባሪው ህወሓት የተፈናቀሉና የወደሙ ተቋማትን ለማቋቋም ከሚያደርጉት ድጋፍ ጎን ለጎን ቡድኑ በህዝብና በሀገር ላይ ያደረሰውን ግፍ ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ እንደሚሰሩ ዳያስፖራዎች አስታወቁ።

በሰሜን አሜሪካና በሱዳን ካርቱም የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ለመልሶ ማቋቋም ሥራው ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉ ደሴ ከተማን ጨምሮ  ደቡብ ወሎ ዞን በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎችና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚውል መሆኑ ተመላክቷል።

በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራ አርቲስቶች አስተባባሪ አርቲስት አልማዝ ጥላሁን እንደገለጸችው አሸባሪው ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች ያደረሰው ጥቃት በእጅጉ አሳዛኝ ነው።

ድርጊቱ የቡድንን አረመኔነት ከነተግባሩ በተጨባጭ ያሳየ መሆኑን ጠቅሳ ዜጎችና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም በእልህና በቁጭት መስራት እንደሚገባ አመልክታለች።

አሸባሪው ህወሓት ያደረሰውን ሁለንተናዊ ጥቃት በስፍራው ሄዳ መመልከቷን የገለጸችው አርቲስቷ  ዳያስፖራው የተፈናቀሉ ወገኖችንና የወደሙ ተቋማትን ለማቋቋም ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ ቡድኑ በህዝብና በሀገር ላይ የፈጸመውን ግፍ ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ እንደሚሰራ አስታውቃለች ።

አንዳንድ የውጭ ሀይሎችና ሀገራት የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ለመቃወም እንደሚሰራም አመላክታለች።

"የኪነ ጥበብ ሙያችንን ተጠቅመን በዜጎች ላይ የደረሰውን የስነ ልቦና ጫና ለማከም ዝግጁ ነን" ስትል አርቲስቷ አክላለች ።

በዛሬው እለት ለወደሙ ተቋማት መጠገኛና ለተቸገሩ ዜጎች የዕለት ደራሽ ምግብ ግዥ የሚውል ከ900 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቃለች።

በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችንም ሆነ ተቋማትን መልሶ በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ዳያስፖራውን በማስተባበር እገዛ እንደምታደርግ አረጋግጣለች።

ከሱዳን ካርቱም የመጡት አቶ አህመድ እንድሪስ በበኩላቸው በካርቱም ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር 733 ሺህ ብር  ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ተቋማትንና የተጎዱ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት ከመደገፍ ባለፈ የአሸባሪውን አረመኔያዊ ተግባር ለዓለም ማህበረሰብ  እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል ።

"አሸባሪው ህወሓት ባደረሰው ዘግናኝ ጥቃት አዝነናል፣ አፍረናልም" ያሉት አቶ አህመድ፣ ዳግም እንዲህ አይነት ጉዳት በህዝብ ላይ እንዳይፈፀም ሁሉም አንድነቱን ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይድ እሸቱና የዞኑ ምክትል አስተዳደሪ አቶ ተስፋ ዳኜ ስለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ህዝቡና ተቋማት እያደረጉ ያለውን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም