በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች አሸንፈው ለመውጣት የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል

155

ጥር 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች አሸንፈው ለመውጣት የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል  ሲሉ የቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በካሜሮን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ዋንጫ የነበረውን ተሳትፎ  አስመልክቶ አሰልጣኝ ውበቱ እና የፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን መግለጫ ሰጥተዋል።

በውድድሩ ደርሶ ለመመለስ ሳይሆን ከምድቡ ለማለፍ እቅድ እንደነበራቸው የገለጹት አሰልጣኝ ውበቱ፤ "በውድድሩ የኢትዮጵያን ህዝብ እና ደጋፊዎችን የሚያስደት ውጤት ለማስመዘግብ የሚቻለውን ሁሉ ጥረት አድርገናል" ብለዋል።

ሆኖም በዝግጅት ጊዜ ማነስ፣ በተጫዋቾች በቀይ ካርድ መውጣት እንዲሁም በቂ የወዳጅነት ጨዋታ ባለማድረግና ሌሎች ተያየዥ ችግሮች ምክንያት የታሰበው አለመሳካቱን ተናግረዋል።

በትላልቅ ውድድሮች ላይ ተጨዋቾች ያላቸው ልምድ አናሳ መሆን ውጤቱ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩንም ጠቅሰዋል።

የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የአካል ብቃት ችግርና የተገኙትን የግብ እድሎች አለመጠቀም ችግር መሆኑን ጠቅሰው፤ በአካል ብቃት በኩል ያለው ችግር የረጅም ጊዜ ስራ እንደሚጠብቀው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን፤ በካሜሪኑ የአፍሪካ ዋንጫ የቡድኑ ከምድብ የማለፍ እቅድን በተለያዩ ምክንያቶች ማሳካት ባለመቻሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን ብለዋል።

በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ከምድብ ጨዋታ የተሰናበተው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2 ጨዋታ ሲሸነፍ በአንድ ጨዋታ አቻ በመውጣት በ1 ነጥብ ወደ አገሩ መመለሱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም