ሊጉ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክርና ኢትዮጵያን በሚጠቅም ተግባር ላይ መስራት አለበት-ዶክተር ዓለሙ ስሜ

84

አዳማ ጥር 17/2014/(ኢዜአ ) የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክርና ኢትዮጵያን በሚጠቅም ተግባር ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ የዴሞክራሲ ማዕከል ግንባታ አስተባባሪ ዶክተር ዓለሙ ስሜ አስገነዘቡ ።

በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀን የተካሄደው የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ስራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ የምክክር መድረክ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫን በማስቀመጥ ዛሬ ተጠናቋል ።

የዴሞክራሲ ማዕከል ግንባታ አስተባባሪ ዶክተር ዓለሙ  ስሜ  በወቅቱ እንዳሉት የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ  አመራርና አባላት በህልውና ዘመቻው የነበረውን ውስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖ በመቋቋም ረገድ  የነበረው አስታዋፆ የጎላ ነበር  ብለዋል ።

"ትናንት ኢትዮጵያን ሲዘርፍና ወጣቱን ሲገድል የነበረ ሃይል ሀገር ለማፍረስ ያለመው ህልም በመላው ህዝብ በተለይም በወጣቱ የጀግንነት ተሳትፎ መክኖ ቀርቷል" ነው ያሉት።

 "ባለፉት ሶስት ዓመታት የኢትዮጵያዊነት ወኔ ዳግም እንዲያንሰራራ  በተሰሩ ስራዎች ወጣቶች ከአራቱም ማዕዘናት በመትመም የኢትዮጵያን ህልውና ማስጠበቅ የቻለ ባለ ታሪክ ሆነዋል" ሲሉም ገልጸው ለ27  ዓመታት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ራሱን ሲያደራጅ የነበረው ሃይል ኢትዮጵያዊነትና ሀገራዊ አንድነት  በመጠናከሩ እራሱ ተበትኖ መቅረቱን አመልክተዋል።

"ማንኛውም የኢትዮጵያ ችግር የጋራችን ነው" ያሉት ዶክተር ዓለሙ  በተለይም ወጣቶች ያደረጉት ተጋድሎ የአሸባሪው ህወሓት የ27 ዓመታት የከፋፍለህ ግዛ ምስጢርን በማጋለጥ ሀገር የማፍረስ ህልሙ ከንቱ ሆኖ እንዲቀር ማድረጉን ጠቁመዋል ።

ወጣቱ በድህረ ጦርነት ወቅትም ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለመሸርሸር በአፍራሽ ሃይሎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን መታገል እንደሚገባው በማስገንዘብ "እሳት ቆስቋሾች እሳት አያይዘው ዞር ሲሉ እንጂ በግንባር ተገኝተው የተፋለሙበት ጊዜና ሰዓት ባለመኖሩ በወጣቶች የሚቀልዱ ማህበራዊ አንቂዎችን በቃችሁ ልንላቸው ይገባል" ሲሉም አሳስበዋል  ።

"አሁንም ጦርነቱ አላበቃም" ያሉት ዶክተር አለሙ  ተላላኪው ሸኔን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች አሁንም ትንኮሳዎች መኖራቸውን ጠቁመዋው "በቀጣይ ኢትዮጵያን ማንም እንዳይደፍራት ለማስቻል አሁን የታየው ሀገራዊ ስሜት መቀዛቀዝ የለበትም"  ሲሉ አሳስበዋል ።

የሀገር መከላከያን የመገንባት ስራ የሚቀጥል በመሆኑ ወጣቱ መከላከያን በሰው ሃይልና ቴክኖሎጂ ለማብቃት በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንደሚገባው እና የሊጉ አመራርና አባላት በቀጣይ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክርና ኢትዮጵያን በሚጠቅም ተግባር ላይ  ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

መንግስት በሀገሪቱ አካታች የሆነ ብሔራዊ ምክክር  እንዲደረግ ቁርጠኝነቱን ከማረጋገጥ ባለፈ አዋጅ፣ ህጎችና አሰራሮችን በማመቻቸት የሀገር ጉዳይ ይመለከተኛል ብሎ የሚያምን አካል ሁሉ እንዲሳተፍበት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የሀገርን ችግር በዘላቂነት በመፍታት ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ ቁርጠኛ ውሳኔዎችንና እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑንም ጠቅሰው ወጣቱ በብሔራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ኢትዮጵያን ጠፍንጎ ከያዛት ችግር ለማውጣት ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም