የዩኒቨርሲቲ - ኢንዱስትሪ ትስስር ችግርን የሚያስቀር የህግ ማዕቀፍ ሊዘጋጅ ነው

54
ሀዋሳ ነሀሴ 24/2010 በድክመት የሚነሳው የዩኒቨርሲቲ - ኢንዱስትሪ ትስስር ችግርን የሚያስቀር የህግ ማዕቀፍ በተያዘው የበጀት ዓመት እንደሚዘጋጅ  የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በሀዋሳ በተካሄደው የሁለቱ ዘርፎች ትስስር የምክክር መድረክ ላይ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንዳሉት የዩኒቨርሲቲ - ኢንዱስትሪ ትስስር የተጀመረው በቅርብ ቢሆንም አሁን በሚፈለግበት ደረጃ አልደረሰም፡፡ ለዚህም ኢንዱስትሪው የዩኒቨርሰሲቲ መምህራንንና ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተማርና በአብሮነት ምርምር ለማድረግ ፍላጎት ማጣት ተጠቅሷል፡፡ መምህራንም ወደ ኢንዱስትሪ ቀርበው ራሳቸውን  ለማብቃትና ለመማር ግደታ አለብኝ ብሎ አለማሰብም ሌላው ክፍተት ነው፡፡ ይህም የሁለቱ ዘርፎች ትስስር ድክመት ያመጣው ችግር መሆኑን ሚኒስትር ዲኤታው አመልክተዋል፡፡ በድክመት የሚነሳውን የዩኒቨርሲቲ - ኢንዱስትሪ ትስስር ችግር የሚያስቀር የህግ ማዕቀፍና በዘርፉ ለሚሳተፉትም የማትግያ ስርዓት በተያዘው  በጀት ዓመት እንደሚዘጋጅ  አስታውቀዋል፡፡ የህግ ማዕቀፉ  ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጡት ትምህርት በተግባር የተደገፈ እንዲሆን ተማሪዎች፣መምህራንና ተማራማሪዎች ወደ ኢንዱስትሪዎች በመሄድ የተግባር ትምህርት እንዲውስዱ ይደረጋል፡፡ ትስስሩ በቀጣይም ወደ  ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የሚያቅፍ ይሆናል ተብሏል፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው ሁለቱ ዘርፎች እስካሁን የተከተሉት ተነጣጥሎ የመስራት ልምድ ስኬታማ እንደሚያደርጋቸው ተናግረው የሚፈላለጉና ተሳስረው ለውጥ እንዲመጡ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሩ እንዳመለከቱት መስሪያ ቤታቸው የዩኒቨርሲቲ - ኢንዱስትሪ ትስስር የጠበቀ እንዲሆን በምርምር እንዲደገፉ በማድረግ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ " 11 የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን የሚገኙት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባሉበት ከተማ ነው " ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ለሊሴ ነሜ ናቸው፡፡ ሆኖም በሚለፈለገው ልክ ልማት ለማምጣት የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር መፍጠር አለመቻሉ በድክመት አንስተዋል፡፡ በኢንዳስትሪ ፓርኮች ዙርያ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጥልቀት ያለውን ጥናትና ምርምር  እንዲያደርጉ ኮርፖሬሽኑ እንደሚፈልግም አመልክተዋል፡፡ በምክክር መድረኩ የተሳተፉ ከ15 ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች ፣  መምህራንና ተመራማሪዎች  የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል፡፡ የፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም ከተማ እንዳሉት ለ19 ሺህ ወጣቶች በፓርኩ ውስጥ የስራ እድል ተፈጥሯል፤ 20 ኩባኒያዎች እያመረቱ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም